በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአሽከርካሪዎች ላይ በተፈጸመ እገታ ተቆጥተው ሰልፍ የወጡ የዐማኑኤል ከተማ ነዋሪዎች ከፖሊስ ጋራ ተጋጩ


በአሽከርካሪዎች ላይ በተፈጸመ እገታ ተቆጥተው ሰልፍ የወጡ የዐማኑኤል ከተማ ነዋሪዎች ከፖሊስ ጋራ ተጋጩ
please wait

No media source currently available

0:00 0:09:20 0:00

በአሽከርካሪዎች ላይ በተፈጸመ እገታ ተቆጥተው ሰልፍ የወጡ የዐማኑኤል ከተማ ነዋሪዎች ከፖሊስ ጋራ ተጋጩ

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ፣ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ “ዓሊዶሮ” በተባለ ቦታ፣ በአሽከርካሪዎች እና በረዳቶቻቸው ላይ የተፈጸመ እገታን ተቃውመው ሰልፍ የወጡ፣ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ማቻከል ወረዳ ዐማኑኤል ከተማ ነዋሪዎች፣ ከፖሊስ ጋራ መጋጨታቸውን፣ ያነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ለአሜሪካ ድምፅ ገለጹ፡፡

እነዚሁ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደተናገሩት፣ ፖሊስ፣ ሰልፉን ለመበተን በወሰደው የኀይል ርምጃ፣ የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉንና አራት ሰዎች መቁሰላቸውን ገልጸዋል፡፡

ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ ለአሜሪካ ድምፅ ሲናገሩ፣ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ፣ በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ታግተዋል፤ የተባሉ አሽከርካሪዎችንና ረዳቶቻቸውን ለማስለቀቅ፣ ቤተሰቦቻቸው የተለያዩ ጥረቶችን እያደረጉ እንደሚገኙ አመልክተዋል። የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት በድርጊቱ ማዘኑን ገልፆ ተጠያቂው መንግሥት ነው ብሏል።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ፣ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ “ዓሊዶሮ” በተባለ ቦታ፣ በአሽከርካሪዎች እና በረዳቶቻቸው ላይ እገታ መፈጸሙን በመቃወም፣ ከትላንት በስቲያ ሰኞ፣ ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም.፣ በምሥራቅ ጎጃም ዞን በማቻከል ወረዳ የዐማኑኤል ወረዳ ነዋሪዎች፣ ሰልፍ መውጣታቸውንና ሰልፉን ለመበተን ፖሊስ በወሰደው የኀይል ርምጃ፣ የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን፣ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉና በቦታው ነበርኹ ያሉ አንድ ግለሰብ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል።

በዋና አውራ ጎዳና መንገዶች ላይ፣ 30 ሰዎች በእንዲህ መልኩ ታግተው መጥፋታቸው፣ ጥያቄ ይፈጥራል። መንግሥት ነኝ ብሎ የተቀመጠው አካል ለምን ሥራውን አይሠራም? በአንድ በኩል፣ ይህን ሕዘብ አስተዳደራለኹ፤ ይላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ ይህ ዐይነት ወንጀል በሕዝቡ ላይ እየተፈጸመ ነው። ይህ በጣም አሳዛኝ ድርጊት ነው፡፡ በእኛ በኩል እንቃወመዋለን፡፡ ይህን፣ በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ላይ ለማሳበብ የሚደረገው ጥረት ግን ሊቆም ይገባል፡፡”

በፖሊስ ርምጃ ስለደረሰው ጉዳት፣ ከደብረ ማርቆስ ሆስፒታል እና ከአካባቢው ባለሥልጣናት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም፡፡

በሰሜን ምዕራብ ሸዋ ዞን “ዓሊዶሮ” በተባለ አካባቢ፣ በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ታግተዋል ከተባሉ፣ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ አሽከርካሪዎች እና ረዳቶቻቸው ውስጥ፣ የአካባቢው ተወላጆች እንደሚገኙበት የገለጹት እማኞቹ፣ ለአንድ ታጋች፣ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር በታጋቾቹ መጠየቁን ተናግረዋል፡፡ የታጋቾቹ ቤተሰቦች፣ የተጠየቁትን የገንዘብ መጠን ከፍለው ለማስለቀቅ እየተሯሯጡ እንደኾነም አመልክተዋል፡፡

አቶ ምስክር ዓምባው የተባሉ ሌላ ግለሰብ፣ በዚኹ “ዓሊዶሮ” እየተባለ በሚጠራው አካባቢ፣ በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት፣ ተደጋጋሚ የእገታ ድርጊት እንደሚፈጸምና ቀደም ሲልም፣ እርሳቸውም የእገታው ሰለባ እንደነበሩና አንድ ሚሊዮን ብር ከፍለው እንደተለቀቁ ነግረውናል፡፡

አቶ ምስክር፣ በቅርቡ፣ ለመንግሥት ሥራ፣ በዐማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ቆይተው ወደ ባሕር ዳር ከተማ፣ ከሁለት የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋራ በመመለስ ላይ እያሉ፣ ከዐዲስ አበባ ወደ ባሕር ዳር በሚወስደው ዋና የአስፋልት መንገድ ላይ፣ በፍቼ እና በገርበ ጉራቻ መካከል በሚገኘው “ዓሊዶሮ” አካባቢ፣ እኩለ ቀን ላይ፣ በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ታጣቂዎች እንደታገቱ ይናገራሉ፡፡

አቶ ምስክር፣ በስድስት ቀናት የእገታ ቆይታቸው፥ አንድ ሕንዳዊን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ታግተው መመልከታቸውንና ከአንድ ሚሊዮን እስከ ሦስት ሚሊዮን ብር እየከፈሉ መለቀቃቸውን አስታውሰዋል፡፡በአጋቾች የተጠየቁትን አንድ ሚሊዮን ብር የከፈሉት፣ የቤተሰቦቻቸውን ቤት ሸጠው እንደኾነ የተናገሩት አቶ ምስክር፣ “በወቅቱ ለክልሉ መንግሥት ስለ ጉዳዩ አመልክቼ የነበረ ቢኾንም፣ እስከ አሁን መልስ የሰጠኝ አካል የለም፤” ይላሉ፡፡

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ፣ ቁጥራቸው ከ30 በላይ የኾኑ አሽከርካሪዎች እና ረዳቶቻቸው፣ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ምዕራብ ሸዋ ዞን “ዓሊዶሮ” በተባለ ቦታ፣ በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት እንደታገቱ፣ ከታጋች ቤተሰቦች መረጃ ደርሶናል፤ ያሉ እማኞች፣ አጋቾቹ፣ ለሹፌሮች፥ አንድ አንድ ሚልየን ብር፣ ለረዳቶች ደግሞ ግማሽ ሚሊዮን ብር በነፍስ ወከፍ ቢከፍሉ እንደሚለቋቸው፣ ለቤተሰቦቻቸው ስልክ በማስደወል መጠየቃቸውን ተናግረዋል፡፡

የታጋቾቹ ቤተሰቦችም፣ በአሁኑ ሰዓት፣ የተጠየቀውን ብር እያሰባሰቡ እንደሚገኙ፣ እማኞቹ አመልክተዋል። እገታውን በተመለከተ፣ ከታጋች ቤተሰቦች መረጃ ለማግኘት ሞክረን፣ በከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንዳሉና ለመናገር ፈቃደኛ እንዳልኾኑ ገልጸውልናል።

የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ዓለም አቀፍ ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ፣ ታጣቂዎቻቸው እንዲህ ዐይነቱን ድርጊት እንዳልፈጸሙ ገልጸው፣ በተጠቀሰው አካባቢ የተለያዩ ኃይሎች እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት የተፈጸሙ ወንጀሎች ሁሉ፣ የመንግሥታዊ ሥርዐቱ ድክመት ውጤት እንደኾኑ ያስረዱት ኦዳ ተርቢ፣ በሥርዓቱ ምክንያት የሚፈጸሙ ወንጀሎችን፣ በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ላይ ማላከክ የተለመደ ኾኗል፤ ብለዋል።

“በዋና አውራ ጎዳና መንገዶች ላይ፣ 30 ሰዎች በእንዲህ መልኩ ታግተው መጥፋታቸው፣ ጥያቄ ይፈጥራል። መንግሥት ነኝ ብሎ የተቀመጠው አካል ለምን ሥራውን አይሠራም? በአንድ በኩል፣ ይህን ሕዘብ አስተዳደራለኹ፤ ይላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ ይህ ዐይነት ወንጀል በሕዝቡ ላይ እየተፈጸመ ነው። ይህ በጣም አሳዛኝ ድርጊት ነው፡፡ በእኛ በኩል እንቃወመዋለን፡፡ ይህን፣ በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ላይ ለማሳበብ የሚደረገው ጥረት ግን ሊቆም ይገባል፡፡”

ከፌዴራል መንግሥት እና ከኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናት፣ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም፡፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ ስለ እገታው መረጃ እንዳለውና በባለሞያዎቹ በኩል በማጣራት ላይ እንደኾነ አመልክቷል፡፡

XS
SM
MD
LG