ዋሺንግተን ዲሲ —
የኋሊት የመጎተት ፍላጎት ያላቸው የጭለማ ኃይሎች የዘላቂ ሰላማችንን ፍሬዎች በማሰናከልና በማበላሸት ሙከራቸው እየተሯሯጡም ቢሆን በታሪካዊው የሰላም ስምምነታችን ታላላቅ ክንዋኔዎች አስመዝግበናል ሲሉ የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር ተናገሩ።
አቶ የማነ ገብረ መስቀል ይህን ያሉት ኢትዮጵያና ኤርትራ የሰላም ስምምነታቸውን አስመራ ላይ የተፈራረሙበትን ሁለተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ቃል ነው።
ሁለቱ ሃገሮች ያከናወኑዋቸው ሥራዎች በማናቸውም ወቅታዊውን ሁኔታ በሚያገናዝብ መስፈርት ታላላቅ ክንዋኔዎች ናቸው ብለዋል።
የቀሩ ሥራዎችም በሁለቱ ሃገሮች የጋራ ቁርጠኝነት የጋራ ራዕይ እና ፖለቲካዊ ፈቃደኝነት ተመርኩዘው እንደሚያሳኩ አያጠራጥርም ሲሉም አክለው አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያና የኤርትራ የሰላም ሂደት ለክልሉ ትብብር አመቺ ድባብ መፍጠሩን አክለው ገልጸዋል።