በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኤርትራ በሰሜን ኢትዮጵያ የምትገኘውን ሽራሮ ከተማ በከባድ መሳሪያ ደበደበች


ፎቶ ፋይል፦ ኤርትራና ኢትዮጵያ ካርታ
ፎቶ ፋይል፦ ኤርትራና ኢትዮጵያ ካርታ

ለመጨረሻ ጊዜ የታደሰ

የኤርትራ ኃይሎች በሰሜን ኢትዮጵያ የምትገኘውን ሽራሮ ከተማ በከባድ መሳሪያ መደብደባቸውን የተባበሩት መንግሥታትንና የአካባቢውን ምንጮች ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል። በድብደባው አንዲት የ14 ዓመት ሴት ልጅ ተገድላ 18 ሰዎች ሲቆስሉ 12 ቤቶች ደግሞ ፈርሰዋል ብሏል የሮይተርስ ዘገባ።

በትግራይ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ለሁለት ወራት አንጻራዊ ሰላም ካገኘ በኋላ በተፈጸመው በዚህ ጥቃት 23 ግዜ ከባድ መሳሪያ መተኮሱንና አንዳንዱ መሳሪያም ተፈናቃይ ቤተሰቦች ያረፉበትን ትምህርት ቤት አንደመታ በሽራሮ ከተማ ያሉ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን ጠቅሶ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የውስጥ መረጃ ልውውጥ ሰነድ ያሰፈረውን መረጃ መመልከቱን ሮይተርስ ጨምሮ ገልጿል።

ከሰነዶቹ አንዱ እንዳሰፈረው በድብደባው አንዲት የ14 ዓመት ሴት ልጅ ተገድላ 18 ሰዎች ሲቆስሉ 12 ቤቶች ደግሞ ፈርሰዋል። የትግራይ ክልልን የሚቆጣጠረው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ የኤርትራ ጦር ቅዳሜና እሁድ ከኤርትራ ድንበር 11 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘውን የሽራሮ ከተማ ሰፍሮ የነበረው ጦራቸውን ደብድቧል ሲል ከሷል።

ኤርትራ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ፌዴራል ጦር ከህወሓት ጋር እአአ 2020 መጨረሻ ጀምሮ ሲያካሂድ ለነበረው ጦርነት ድጋፍ መስጠቷን አስታውሷል ሪፖርቱ።

በሳምንቱ መጨረሻ ባገረሸው ግጭት አራት የኤርትራ አዛዦችንና ከ300 በላይ ወታደሮችን መግደላቸውን ህወሓት በበኩሉ አስታውቋል። የሮይተርስ ዘገባ አክሎም ከኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል አስተያየታቸውን ለማግኘት አለመቻሉንና በህወሓት የተጠቀሱትን ቁጥሮች በገለልተኛ ወገን ማጣራት እንዳልቻለ ጠቅሷል።

“ውጥረቱን ለመጨመርና እኛን እርምጃ እንድንወስድ ለመገፋፋት የሽራሮ ከተማን በግንቦት 28 እና 29 ድብድበዋል” ብለዋል የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ በትዊተር መልዕክታቸው።

የኢትዮጵያ ሰራዊት ቃል አቀባይ ኮሎኔል ጌትነት አዳነንና እና የመንግሥት ቃል አቀባይ ለገሰ ቱሉን ሃሳብ ለማካተት መልስ ባለመስጠታቸው ምክንያት አለመቻሉን ሮይተርስ አስታውቋል።

የኢትዮጵያና የኤርትራ ጦሮች በ2021 አጋማሽ ላይ ከትግራይ ሲወጡ የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ ባለፈው መጋቢት የተናጥል ተኩስ አቁም ማወጁ የታወሳል።

ይህም ረሃብ ወደመታት ትግራይ እርዳታ እንዲገባ ማስቻሉንና የሺህዎችን ህይወት ቀጥፎ ሚሊዮኖችን ያፈናቀልው ጦርነት ጋብ እንዲል አድርጓል። ሆኖም ግን በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በመንግሥታቸው መገናኛ ብዙሃን እንዳስታወቁት የትግራይ ጦር ሃገራቸውን የሚያጠቃ ከሆነ ወይም የኢትዮጵያን መረጋጋት የሚያውክ ትግባር ከፈፀመ መልሰው ጣልቃ እንገባለን ማለታቸውን ሮይተርስ ጨምሮ ገልጿል።

በአሜሪካ ድምፅ በኩል የኤርትራንም ሆነ የኢትዮጵያ መንግስትን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።

የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስቴር በድህረ ገጹ ዓርብ ዕለት ባወጣው መግለጫ ህወሓት በአሁኑ ወቅት የማያቋርጥ የጦር ከበሮውን እየደለቀና በኢትዮጵያና በኤርትራ ላይ ሦስተኛ ጥቃት ለመሰንዘር እየተዘጋጀ እንደሆነ፤ እንዲሁም የምግብ ዕርዳታውን ወታደሮችን ለመመልመል እየተጠቀመበት ነው ብሏል።

በሌላ በኩል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ አል ዐይን ለተባለ የሃገር ውስጥ ሚዲያ በሰጡት መግለጫ፣

“በህወሓትና በኤርትራ መካከል ያለው መካረርና አልፎ አልፎ እየተደረገ ያለው ውጊያ፤ ኢትዮጵያ እና ኤርትራን ወደጦርነት ሊያስገባ አይችልም ወይ?” በሚል ለቀረበላችው ጥያቄ፣

“ወደዚያ የሚያመራ ሁኔታ እንደሌለና ህወሓት ትንኮሳውን የሚፈፅመው ሁለቱን ሀገራት ወደ ግጭት ለማስገባት እንደሆነ ገልጸው ይህ ግን መቼም ቢሆን ‘አይሳከም’ ማለታቸውን ዘግቧል።

የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ በትዊተር መልዕክታቸው ኤርትራ ባለፈው ማክሰኞ በ57ኛና በ21ኛ ክፍለ ጦሯ የፈጸመችውን ጥቃት የህወሓት ጦር ማክሸፉንና የተላኩትም አጥቂዎች በተደረገው የመልሶ ማጥቃት መደምሰሳችውን ጽፈዋል።

XS
SM
MD
LG