ዋሽንግተን ዲሲ —
“የኤርትራ መንግሥት ዜጎችን መበዝበዝና በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ማሰማራቱን እንዲያቆምና ዓለም አቀፍ ግዴታውን እንዲወጣት ዩናይትድ ስቴትስ ታሳስባለች” ሲል አስመራ የሚገኘው ኤምባሲዋ ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ኤምባሲው ባወጣው መግለጫ “የኤርትራ መንግሥት የግዳጅ ብሄራዊ ውትድርናና የዜግነት ሚሊሻ በመሳሰሉ አስገዳጅ የሥራ መስኮች ዜጎችን ላልተወሰነ ጊዜ ወይም እንዳሻው በዘፈቀደ ያሰማራል” ብሏል።
“ዩናይትድ ስቴትስ ከኤርትራ ህዝብ ጎን ትቆማለች” ያለው የኤምባሲው መግለጫ “በአዋጅ 11/199 የወጣው የብሄራዊ ውትድርና አዋጅ ለ18 ወራት ብቻ” እንደሚሆን አመልክቷል።
የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረመስቀል ባለፈው ዓርብ ባወጡት የትዊት መልዕክት “የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በየጊዜው ኤርትራ ላይ የሚቆልለው ክስ ወሰን የለውም” ብለዋል።
“ኤርትራ ሯሷ ተጠቂ ናት እንጂ ህግ ወጥ የሰዎች አስተላላፊ ድርጅት አይደለችም” ያሉት የማስታወቂያ ሚኒስትሩ “የተባበሩት መንግሥታት ይህን ነገር እንዲመረምር ስታሳስብ ቆይታለች፡፡ ይሁን እንጂ ዋሽንግተን አሁንም ኤርትራን ይህን ለመዋጋት በቂ ጥረት ባላደረጉ አገሮች ጥቁር መዝገብ ውስጥ ጨምራታለች” በማለት ወቀሳቸውን አሰምተዋል፡፡