በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲያደርግ ሂዩማን ራይትስ ዎች ጠየቀ


“የኢትዮጵያ መንግስት የመብት ጥበቃን አስመልክቶ ተጨባጭ መሻሻል ያሳይ ዘንድ የአውሮፓ ሕብረት ግፊት ማድረግ አለበት” ሲል ሂዩማን ራይትስ ዎች ባለፈው አርብ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ብራስልስ ላይ በሚሰበሰቡት ወቅት የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖረው ግንኙነት አቅጣጫ መሪዎቹ ከሚነጋገረባቸው ዋነኛ አጀንዳዎች አንዱ ይሆናል” ያለው የሂዩማን ራይትስ ዎች መግለጫ፤ ስብሰባው በሚካሄድበት ወቅት በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል የጀመረው እና በሰላማዊ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ውድመት ያስከተለው ጦርነት 19ኛ ወሩን እንደሚስቆጥር አመልክቷል።
መግለጫው አክሎም “የኢትዮጵያ መንግስት በሺዎች የተቆጠሩ የትግራይ ተወላጆችን በዘፈቀደ ለማሰር ተጠቀመበት” ያለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባለፈው የካቲት ወር ማንሳቱን እና ካለፈው ሚያዝያ ወር አንስቶም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው እርዳታ የጫኑ ከባድ መኪኖች ወደ ትግራይ እንዲገቡ ማድረጉን አስታውሷል።
“ሆኖም በሰሜን ኢትዮጵያ ግፍ እና ስቃዩ አሁንም ቀጥሏል።“ ያለው መግለጫ፡ “ለአንድ ዓመት ያህል መንግስት በትግራይ የምግብ፣ ነዳጅ እና ሌሎች አስፈላጊ አቅርቦቶችን በመገደብ የመገናኛ፣ የባንክ እና የመብራት አገልግሎቶችንም ፍጹም ዝግ አድርጎ ቆይቷል።” ብሏል።
“ተጨማሪ ዕርዳታ እንዲገባ ቢፈቀድም፣ መጠኑ አሁንም ከሕዝቡ ፍላጎት ያነሰ ነው” ያለው ሂዩማን ራይትስ ዎች “ይህም ማለት በተለይ የመድኃኒት አቅርቦቶች እና አገልግሎቶች እጦት ሥር የሰደደ ሕመም ያለባቸውን እና በጦርነት ወቅት ለወሲባዊ ጥቃት የተጋለጡትን ጨምሮ ከጥቃት የተረፉ ወገኖች አስፈላጊውን እንክብካቤ አያገኙም ማለት ነው።” ብሏል።
“የአውሮፓ ህብረት የሚያደርገው ጫና ክብደት እንዲኖረው፣ ትኩረቱ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ማስቆም ላይ መሆን አለበት።” ሲል የቀጠለው መግለጫ አያይዞም “ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች እና ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የሚደረጉ ሌሎች ግንኙነቶች በራሳቸው ግብ ሳይሆኑ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የሰላማዊ ዜጎችን ደህንነት በማስጠበቅ ረገድ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት መሳሪያ መሆን አለባቸው” ብሏል።
“የአውሮፓ ህብረት በዓለም ዙሪያ በሚፈጸሙ የጦር ወንጀሎች ተጠያቂ በሆኑ ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ ሲወስድ ዓለም እያየ ባለበት “በአፍሪካ ቀንድ ቀላል መሆን የለበትም።” ብሏል።

XS
SM
MD
LG