በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በካሜሩን በጎርፍ ምክንያት በተከሰተ ኮሌራ 17 ሠዎች ሞቱ


ፎቶ ፋይል፦ ካሜሩን
ፎቶ ፋይል፦ ካሜሩን

ካሜሩንን ከናይጄሪያና ቻድ ጋር በሰሜን በሚያዋስነው አካባቢ የደረሰውን የጎርፍ ፣መጥለቅለቅ ተከትሎ በተቀቀሰው የኮሌራ ወረርሽኝ 17 ሠዎች መሞታቸው ተገለጸ። ለመድረስ አስቸጋሪ በሆኑ መንደሮች በአንድ ሳምንት ውስጥ ሌሎች በርካቶች ሳይሞቱ አይቀርም የሚል ስጋትም አሳድሯል።

የመንግስት ባለሥልጣናትና የዕርዳታ ድርጅቶች ዛሬ ባደረጉት ስብሰባ፣ የሰብዓዊ ሠራተኞች ከናይጄሪያ ጋር በሚያዋስነው አካባቢ ባሉ የተጨናነቁ ሆስፒታሎች እንዲሠማሩ ወስነዋል።

የአሜሪካ ድምጹ ሞኪ ኤድዊን ኪንዴዝካ ከያውንዴ በላከው ዘገባ እንደጠቆመው፣ ሃገሪቱን ከናይጄሪያ ጋር ከሚያዋስናት ድንበር አካባቢ በወረርሽኙ የተጠቁ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠዎች መኖራቸውን የጤና ጥበቃ ባለሥልጣናቷ አስታውቀዋል። እስካሁን የ17 ሠዎች ህይወት ሲያልፍ በየሆስፒታሉ በመረዳት ላይ የሚገኙ ሌሎች በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ መሆናቸውም ተመልክቷል።

እንደ መንግስቱም ገለጣ፣ የሰብዓዊ ሠራተኞች በማይደርሱባቸው መንደሮችና ከተሞች በወረርሽኙ የተያዙና ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ሊሆን ይችላል።

ሀገሪቱን ከናይጄሪያና ከቻድ ጋር በሚያዋስኑ እና ቦኮ ሃራም አሸባሪ ቡድን ጥቃት በተከታታይ የሚያደርስባቸው የሰሜኑ የአገሪቱ አካባባዎች የዕርዳታ ሠራተኞች በበሽታው የተጠቁትን ለመርዳት እንዳይችሉ ማድረጉንም ባለስልጣናቱ አመልክተዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ እስከያዝነው ወር ድረስ፣ ናይጄሪያን ከቻድና ከካሜሩን በሚያዋስኑ ሦስት ግዛቶች ከ1ሺህ በላይ ሰዎች ለኮሌራ ወረርሽኝ መጋለጣቸው ታውቋል።

XS
SM
MD
LG