የካሜሩን የጦር ኃይል በቅርቡ የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ሽምቅ ተዋጊዎች ሃምሳ አምስት ሰዎች መጥለፋቸውን ተከትሎ በመቶዎች የተቆጠሩ ወታደሮች ድንበሩ ላይ አስፍሯል።
አማጽያኑ ነጋዴዎችን፣ ገበሬዎችን እና ከብት አርቢዎችን ዒላማ እያደረጉ ንብረት እና ገንዘብ እንደሚዘርፉ የካሜሩን የጦር ሰራዊት ተናግሯል። አማጽያኑ ያገቷቸውን ሰላማዊ ሰዎች ለማስለቀቅ ትናንት ሰኞ ብዛት ያላቸው ወታደሮች በምስራቁ የድንበር አካባቢ ወዳሉ መንደሮች እና ደኖች ማሰማራቱን የካሜሩን የጦር ኃይል ገልጿል።
ታጋቾቹን ለማስለቀቅ የተሰማራውን ኃይል የመሪት የካሜሩኑ ኮሎኔል ዶሚኒክ ኢንጆካ ታጣቂዎቹ ሁለቱን ታጋቾች ስንደርስባቸው ተኩስ ከፍተው ገድለዋል።
ሰባት ታጋቾች አስለቅቀን ማውጣት ችለናል ብለዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ (ሚኑስካ) እንዳለው ከሀገሪቱ ወታደሮች ጋር በሚካሄደው ውጊያ ከበርካታ ከተሞች የተባረሩ ታጣቂዎች ከካሜሩን ጋር በሚዋስነው የድንበር አካባቢ ተደብቀዋል።