ዋሽንግተን ዲሲ —
የቡርኪና ፋሶ ወታደሮች የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ሮች ማርክ ክርስቲያን ካቦሬንና የእርሳቸውን ባለሥልጣኖች በቁጥጥር ሥር የማዋላቸውን ዜና ተከትሎ ነዋሪዎቹ በአገሪቱ ዋና መዲና በመውጣት ደስታቸውን እየገለጹ መሆኑ ተሰማ፡፡
የወታደሮቹ እምርጃ የመጣው የቡርኪና ፋሶ ህዝብ የፕሬዚዳንቱ አስተዳደር የእስላማዊ አማፅያንን አያያዝ በመቃወም የተቃውሞ ሰልፍ በተጠራ ማግስት መሆኑ ታውቋል፡፡
በሰሜን የአገሪቱ ክፍል ይንቀሳቀሳሉ የተባሉት ፅንፈኞቹ የእስላማዊ መንግሥት አማፅያን 49 የመንግሥት ወታደሮችን ከገደሉበት ጊዜ ጀምሮ በጦሩ አባላት ዘንድ በተፈጠረ ቅሬታ መፈንቅለ መንግሥት ሊካሄድ ይችላል የሚል ወሬ ሲነገር መቆየቱ ተገልጿል፡፡
በዋና ከተማው ኦጋዱጉ በሚገኘው ቤተ-መንግሥት አቅራቢያ የተኩስ ድምፅ መሰማስቱም በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
የቡርኪና ፋሶው እንደ መፈንቅለ መንግሥት ከተወሰደ፣ ባለፉት 18 ወራት በምዕራብ አፍሪካ ማሊና ጊኒን ተከትሎ ሦስተኛው ሊሆን እንደሚችል ተመልክቷል፡፡