የብሪታንያ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ሠራተኞች በአስርት ዓመታት ውስጥ ያልታየ ነው የተባለ ግዙፍ የሥራ ማቆም አድማ ዛሬ ጀመሩ።
የድርጅቱ ሥራ አመራር እና የባቡር፣ የባህር እና የመንገድ ትራንስፖርት ሰራተኞች ማህበር በሠራተኞች የደሞዝ ክፍያ መጠን እና ከሥራ ዋስትና ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ዙሪያ የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት እና የሥራ ማቆም አድማውን ለማስቀረት በታለመ ጥረት ትናንት ሰኞ ያደረጉት የመጨረሻ ደቂቃ ውይይት ሳይሰምር ቀርቷል።
እንደ ሠራተኛ ማኅበራት መሪዎቹ ገለጣም የሠራተኞች ደሞዝ የዋጋ ከተፈጠረው የዋጋ ግሽበት ጋር ሊሄድ አልቻለም።
የብሪታንያው የትራንስፖርት ሚኒስትር ግራንት ሻፕስ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት “አድማው መጠነ ሰፊ ማስተጓጎል ይፈጥራል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ከ40ሺህ በላይ አባላት ያሉት አንድ ሌላ የሠራተኛ ማኅበር የፊታችን ሃሙስ እና ቅዳሜ ተመሳሳይ የሥራ ማቆም አድማ ለማድረግ ማቀዱ ታውቋል።