በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዩክሬኑ ጦርነት እንዲያበቃ ባይደን ከፑቲን ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ ናቸው


የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እና የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እና የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን

ለፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ትናንት በነጩ ቤተ መንግሥታቸው ብሄራዊ የእራት ምሽት ያሰናዱት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን 10 ወራትን ያስቆጠረው የሩሲያ ዩክሬን ወረራ እንዲቆም ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ባይደን እስካሁን ከፑቲን በኩል ምንም ዓይነት ፍላጎት አለማየታቸውን ተናግረዋል፡፡

ባይደን ይህን የተናገሩት ከፕሬዚዳንት ማክሮን ጋር በዩክሬን እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ በነጩ ቤተ መንግሥት ለሰዓታት በዝግ ከመከሩ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ነው፡፡

“ከፑቲን ጋር ለመነጋገር ተዘጋጅቻለሁ፡፡ ይህን የማደርገው ግን ከኔቶ ጋር በመምክር ብቻ ነው” ያሉት ባይደን ይሁን እንጂ “ፑቲንን በቶሎ አግኝቶ የማነጋገር እቅድ የለኝም፡፡ ያ ለብቻዬ በራሴ የማደርገውም ነገር አይደለም” ብለዋል፡፡

“ይህን ጦርነት ለማቆም ያለው አንድ መንገድ ብቻ ነው” ብለዋል ባይደን፡፡

“ፑቲን ከዩክሬን ለቀው መውጣት አለባቸው፤ (ፑቲን) የሚያደርጉት ነገር ያማል፡፡ ጦርነቱን የሚያቆሙበትን መንገድ የሚፈልጉ ከሆነ ያንን እያደረጉ አይደሉም” ሲሉም ፕሬዚዳንቱ አክለዋል፡፡

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን የምትስጠውን ተጨማሪ ወታደራዊ እና ሰብአዊ እርዳታ ትቀጥልበታለች ብለው እንደሚተማመኑ ገልጸዋል፡፡

ይህ “ስለ እሴታችን የምናደርገው ነው” ያሉት ማክሮን “ዩናይትድ ስቴትስ ዩክሬንን መርዳቷ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው” ብለዋል፡፡

ጦርነቱን ለማቆም “ዩክሬን እንድተገብር” ዩናይትድ ስቴትስ በፍጹም አትፈቅድም” ሲሉ የተናገሩት ባይደን የኪየቭ መንግሥት ይሁንታ ሳይኖርበት ምንም ነገር እንደማይፈጸም አስታውቀዋል፡፡

ባይደን ቀደም ሲል በሰጡት መግለጫ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በባይደን የፕሬዚዳንትነት ዘመን ብሄራዊ የእራት መስተንግዶ የተደረገላቸው የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸውላቸዋል፡፡

XS
SM
MD
LG