በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ባይደን የቴክሳሱን ጥቃት ተከትሎ መሣሪያ አምራች ኢንዱስትሪውን መጋፈጥ አለብን አሉ


ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን

ዩናይትድ ስቴትስ ቴክሳስ ክፍለ ግዛት ውስጥ በሚገኝ ትምህርት ቤት ተኩስ በከፈተ አጥቂ እጅ አስራ ዘጠኝ ተማሪ ልጆች እና ሁለት አዋቂዎች መገደላቸውን ተከትሎ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን

"የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት የመሳሪያ ቁጥጥር ህግጋቱን እንዲያሻሽል ግፊት አደርጋለሁ።" በማለት ፊታቸው ላይ በግልፅ ቁጣ እና ሀዘን እየተነበባቸው ቃል ገብተዋል። የአሜሪካ ድምጿ አኒታ ፓወል እና ክሪስ ሃና ዘገባውን አጠናቅራለች።

ደቡብ ምዕራባዊ ዩናይትድ ስቴትስ ቴክሳስ ክፍል ግዛት ዩቫልዲ ከተማ ውስጥ ትናንት ማክሰኞ የደረሰው ይህ ግድያው በሀገሪቱ ታሪክ በትምህርት ቤት ውስጥ በተከፈተ ተኩስ የብዙ ሰው ህይወት ከጠፋባቸው የጅምላ ጥቃቶች አንዱ ነው።

ባለሥልጣናቱ እንዳሉት የአስራ ስምንት ዓመቱ አጥቂ መጀመሪያ ሴት አያቱን ከገደለ በኋላ መኪናውን እየነዳ ሄዶ ትምህርት ቤቱ ደጃፍ ላይ አጋጭቶ በመውረድ ትምህርት ቤቱ ውስጥ ገብቶ ተኩስ የከፈተ ሲሆን አጥቂውን ህግ አስከባሪዎች ተኩሰው ገድለውታል።

የቴክሳስ የህዝብ ደህንነት ጥበቃ አባል ሳጅን ኤሪክ ኤስትራዳ ለሲኤንኤን በሰጡት ቃል የጥይት መከላከያ የለበሰው አጥቂው መሣሪያውን ይዞ ካጋጨው መኪና ውስጥ ወጥቶ ሲራመድ ህግ አስከባሪዎች አይተውት ቢከታተሉም ትምህርት ቤቱ ውስጥ እንደገባ ገልጸዋል።

ትናንት ማታ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን "ተገቢ የመሳሪያ ቁጥጥር ህግ " ሲሉ የገለጹት እንዲደነገግ የሚያስችል ትርጉም ያለው ዕርምጃ እንደሚወስዱ ቃል ገብተዋል።

ባይደን የቴክሳሱን ጥቃት ተከትሎ መሣሪያ አምራች ኢንዱስትሪውን መጋፈጥ አለብን አሉ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:38 0:00

"የአስራ ስምንት ዓመት ልጅ መሳሪያ የሚሸጥበት መደብር ገብቶ ሁለት አውቶማቲክ ጠብመንጃ ለመግዛት መቻሉን አስቡት፣ ልክ እኮ አይደለም። እንዲያው ስለእግዚአብሔር አንድ ሰው ሰው ሊገድልበት ካልሆነ ከባድ መሣሪያ ለምን ያስፈልገዋል። ስለእግዚአብሔር ጫካ ውስጥ ጥይት የማይበሳው ሰደሪያ ለብሶ የሚሮጥ አጋዘን የለ!! በጣም እኮ የሚያናድድ ነገር ነው።" ያሉት ፕሬዚዳንቱ በማስከተል

“መሣሪያ አምራቾቹ ትልቅ ትርፍ የሚያስገኝላቸው ስለሆነ ከባድ መሣሪያ እንዲሸጥላቸው ሃያ ዓመት ሙሉ በጣም ሰርተውበታል። ስለእግዚአብሔር በርትተን ይህን ኢንዱስትሪ መጋፈጥ አለብን።" ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ባይደን ሮብ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተፈጸመው ጥቃት የሚወዱዋቸው ለተገደሉባቸው ቤተሰቦች ሀዘናቸውን የገለፁ ሲሆን

"የልጅ ሞት ከነፍስህ አንዳች ክፋይ ምንጭቅ ተደርጎ ሲሄድ እንደማለት ነው። ውስጥን ባዶ ያደርጋል። አንዳች እፍን አድርጎ የሚይዝ ነገር አለው። እስከዘላለሙ አብሮ የሚኖር የማይለቅቅ ሀዘን ነው። የሚፈጥረው የተለየ ስሜት ነው።" ብለዋል።

በትምህርት ቤቱ ላይ የጅምላ ተኩስ የከፈተው አጥቂ የዩቫልዴ ከተማ ነዋሪ የአስራ ስምንት ዓመት ወጣት እንደነበር እና የጸጥታ ጥባቂዎች እንደገደሉት ትናንት ሪፐብሊካኑ የቴክሳስ አገረ ገዢ ግሬግ አበት ገልጸዋል።

"ዩቫልዲ ውስጥ የደረሰው በጣም የሚሰቀጥጥ እና የሚያሳዝን ነገር ነው። ቴክሳስ እንዲህ ላለ አድራጎት ትዕግሥት ሊኖራት አይችልም። የከተማዋ ህግ አስከባሪዎች እና የቴክሳስ ክፍለ ሀገር የህዝብ ደህንነት ጥበቃ አባላት ፈጣን ዕርምጃ በመውሰድ ላይ ናቸው። ጥቃቱን ያደረሰውን ሰው ማንነት ለይተዋል፣ ሞቷል።" ብለዋል።

በዋሽንግተን የፕሬዚዳንት ባይደን ዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት የቴክሳሱን ጥቃት ወደፊት እንዲህ ያለ ጥቃት እንዳይደርስ የሚከላከል የለውጥ ዕርምጃ ጥሪ አድርገው ወስደውታል።

ዲሞክራቱ ሴኔተር ክሪስ መርፊ "ባልደረቦቼን እዚህ መድረክ ላይ ተንበርክኬ እለምናችኋለሁ። ይሄን ጉዳይ ወደፊት የሚያራምድ መላ ፈልጉ። አብረን እንዲህ ያለው ነገር እንዳይፈጸም የሚረዳ ህግ ለማውጣት የምንችልበትን መንገድ እንፈልግ። ሪፐብሊካን ባልደረቦቼ እኔ የምደግፈውን ሁሉንም ነገር እንዲደግፉ አልጠብቅም እሱን እረዳለሁ። ነገር ግን ሁላችንንም የሚያስማማን አንድ ነገር ይኖራል እና እንፈልግ።

አሜሪካ ውስጥ የጅምላ ጥቃት ከእንግዲህ ፈጽሞ እንዳይደገም ዋስትና ላይሰጥ ይችላል። አንድ ሥምምነት ላይ መድረስ ግን እንችላለን።" በማለት ተማጽኖ አሰምተዋል።

ቴክሳስ የመሣሪያ ባለቤትነት መብት እንዳይነካ አጥብቃ የምትከራከር መሆንዋን በኩራት ነው የምትመለከተው። ነዋሪዎቹዋ ብዙ ጊዜ ዕውነትም ባይሆን "ሰንደቅ ዓላማዋ ከዩናይትድ ስቴትስ ባንዲራ እኩል ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ የተፈቀደላት ብቸኛ ስቴት" ብለው ሲገልጿት ይሰማሉ።

ፕሬዚዳንት ባይደን በዋይት ሀውስ እና በሁሉም የመንግሥት ህንጻዎች ብሄራዊው ሰንደቅ አላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ በቴክሳስ ዩቫልዲ ከተማ ትምህርት ቤት በደረሰው አረመኒያዊ የጅምላ ግድያ በጥልቅ ማዘናቸውን ቃል አቀባያቸው ገልጸዋል። አብዛኞቹ የጥቃቱ ሰለባዎች ልጆች መሆናቸው ደግሞ አብዝቶ የሚያሳዝን ነው ብለዋል።

XS
SM
MD
LG