ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ዛሬ ሀሙስ በተካሄደውና በአዲስ አስተዳደር በተቋቋመው፣ ዓመታዊው “ብሄራዊ የፀሎት ጠዋት ቁርስ” ላይ የአንድነት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ባይደን በንግግራቸው “በፖለቲካችን እና በህይወታችን ሁል ጊዜም እርስ በርሳችን የምንተያየው እንደተፎካካሪዎች ሳይሆን እንደ ባላንጣዎች ነው፡፡ እርስ በርስ የምንተያየው እንደ ጠላቶች እንጂ እንደ ጎረቤታሞች አይደለም” ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም “ይህ ጊዜ እጅግ አስቸጋሪ የሆነውን ያህል፣ ቀረብ ብለን ብናይ፣ ጥናካሬንና አሜሪካንን ለረጅም ዘመን የሚገልጻትን ቁርጠኝነት እንመለከታለን” በማለት ተናግረዋል፡፡
ብሄራዊ የፀሎት ጠዋት ቁርስ የተካሄደው፣ በካፒቶል የጎብኝዎች ማዕከል ሲሆን፣ 450 ሰዎችን በሚይዘው አዳራሽ የሚገኙ መቀመጫዎች በምክር ቤት አባላት፣ በመንግሥት ባለሥልጥናትና በሌሎች ሰዎች ተሞልተው እንደነበር ተገልጿል፡፡
ዓመታዊ ሥነ ሥርዓቱ የተካሄደው አዘጋጁ አካልና አመራር ከአወዛገበው የግል ሃይማኖት ቡድን ራሱን ለማራቅ ከወሰነ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ሥነ ሥርዓቱን አሁን ያዘጋጀው፣ በቀድሞ የምክር ቤት አባላት በሚመራው አዲሱ ቡድን የተቋቋመው፣ ብሄራዊ የጸሎት ጠዋት ፋውንዴሽን መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ዓለም አቀፉ ፋውንዴሽ፣ የራሱን ሥነ ሥርዓት የባይደን ንግግር በርቀት በሚሰማበትና በአቅራቢያው በሚገኝ ሆቴል ውስጥ እያካሄደ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ባይደን በሌላኛው አዳራሽ ውስጥ የሚገኙትንም ሰዎች ብዛት ባመለከቱበት ንግግራቸው “ሁላችሁም 1ሺ ሶስት መቶዎቻችሁ፣ እንኳን ደህና መጣችሁ” ብለዋል፡፡
በዝግጅቱ ላይ ባይደን ከመጋረጃው በስተጀርባ ለውጥ መኖሩን እውቅና ሰጥተው ያመለከቱበት ብቸኛው አጋጣሚ መሆኑም ተመልክቷል፡፡
ዝግጅቱ በተቃራኒ ጎራ ያሉትን ሰዎች አንድ ላይ ለማምጣት ታቅዶ የተዘጋጀ ሲሆን ባይደን ከካሊፎርኒያው ሪፐብሊካን የተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ኬቭን መካርቲ ጎን ተቀምጠው ታይተዋል፡፡
ሁለቱ መሪዎች የአገሪቱን (የመንግሥትን) የመበደር ጣራ እንዲጨምር ለመወሰንና አገሪቱን ከዕዳ ውድቀት ለመታደግ በሚቻልበት ሁኔታ እየተወዛገቡ መሆኑ ይታወቃል፡፡
“ትናንት ጥሩ ስብሰባ ነበረን” በማለት ባይደን ስለ መካርቲ የተናገሩ ሲሆን” ሁለቱም “እርስ በርስ ለመከባበር” እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡