በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ባይደን ከዩክሬን ፕሬዚዳንት ጋር ተነጋገሩ አጋርነታቸውን ገለጹ


ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በዊልሚንግተን ዴል ከሚገኘው የግል መኖሪያ ቤታቸው በስልክ ሲወያዩ፣ እአአ ዴሴምበር 30/2021
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በዊልሚንግተን ዴል ከሚገኘው የግል መኖሪያ ቤታቸው በስልክ ሲወያዩ፣ እአአ ዴሴምበር 30/2021

ሩሲያ ዩክሬንን ብትወር “የማያሻማ ምላሽ” እንሰጣለን አሉ

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከዩክሬን ፕሬዚዳንት ጋር ትናንት እሁድ ባደረጉት የስልክ ውይይት ሩሲያ ዩክሬንን ለመውረር ተጨማሪ እምርጃ ብትወሰድ ዩናይትድ ስቴትስና ተባባሪዎችዋ “የማያሻማ ምላሽ ይሰጣሉ” ሲሉ ለዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ የነገሯቸው መሆኑን ተገለጸ፡፡

የዋይት ኃውስ ባለሥልጣናት በሰጡት መግለጫ፣ ሁለቱ መሪዎች በዩክሬን ድንበር አቅራቢያ ግዙፍ ሠራዊቷን ያከማቸችው ሩሲያ የፈጠረችውን ውጥረት ለማርገብ፣ ሌሎች የዲፕሎማሲ አማራጮችንም ለማየት ጥረት ለማድረግ መወያየታቸውንም ተናግረዋል፡፡

ከሁለቱ መሪዎች የስልክ ውይይት በኋላ መግለጫ ያወጡት የዋይት ኃውስ ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ

“ባይደን ለዩክሬን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት እንዲጠበቅ ዩናይትድ ስቴትስ ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠውላቸዋል” ብለዋል፡፡

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ከውይይቱ በኋላ ባወጡት የትዊት መልዕክት፣ ሁለቱ መሪዎች በዩክሬን፣ ዩናትይድ ስቴትስና ተባበሪዎችዋ አማካይነት፣ የአውሮፓን ሰላም ለመጠበቅ ተጨማሪ ውጥረት እንዳይፈጠር ለማድረግና የግዛት መዋቅር ለውጥና የጠቅላይነት ስሜት እንዳይኖር ለማድረግ የጋራ እርምጃዎችን ስለሚወስዱበት መንገድ መወያየታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ዘለንስኪ የዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን የምትሰጠውን የማያወላውል ድጋፍም እናደንቃለን ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ባይደን 100ሺ ጦሯቸውን በቀድሞዪቷ የሶቭየት ኀብረት ግዛት ዩክሬን ድንበር ያስፈሩትን የሩሲያውን ፕሬዚዳንት ቭላድሚየር ፑትን ሀሳብ ለማስለወጥ ያስገኙት ለውጥ ብዙም አለመሆኑ ተመልክቷል፡፡

የሩሲያና የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንቶች ባላፈው ሀሙስ 50 ደቂቃ የፈጀ የስልክ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ሩሲያ ዩክሬንን የምትወር ከሆነ ጠንካራ የምጣኔ ሀብት ማዕቀብ የሚጠብቃት መሆኑን ነግረዋቸዋል፡፡

ባይደን ባላፈው ወር በሰጡት መግለጫ ወታደራዊ እምርጃን እንደ አማራጭነት እንደማይጠቀሙ ገልጸዋል፡፡

ሞስኮ የዩክሬን አካል የነበረችው ክሬሚያን እኤአ በ2014 ወደ ራሷ ግዛት መጠቅለሏ የሚታወስ ሲሆን ምዕራባውያን ተቃውሟቸውን የገለጹት ብዙም ጉዳት ያላስከተለባትን ማዕቀብ በመጣል ብቻ እንደነበር ተመልክቷል፡፡

ሩሲያ ባለፈው ሳምንት ባወጣችው መግለጫ፣ “ዩናይትድ ስቴትስ ሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ብትጥል የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ ይሰብረዋል” ማለቷ ይታወሳል፡፡

XS
SM
MD
LG