የዩናይትድ ስቴትሱ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስትን፣ የሶማሊያውን ፕሬዝደንት ሃሳን ሼክ ሞሃሙድ ትናንት በፔንታጎን ተቀብለው አነጋግረዋል።
ሁለቱ ወገኖች በመከላከያ ትብብር እና በቀጠናው ባሉ የጸጥታ ስጋቶች ላይ ተነጋግረዋል።
ሶማሊያ በአሁኑ ወቅት በአል ሻባብ ላይ የምታደርገውን ዘመቻ እና ሶማሊያውያን በመክፈል ላይ ያሉትን መስዋትነት ሎይድ ኦስትን አድንቀዋል። በማዕከላዊ ሶማሊያ በአል ሻባብ ላይ የተደረገው ውጤታማ ዘመቻ እና ቀጣይነት ያለው ድል እንዳበረታታቸውን ኦስትን ገልጸዋል።
በሶማሊያ የሚገኘውን የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል ለመቀነስ ዝግጅት በሚደረግበት በዚህ ወቅት፣ የዓለም አቀፍ ድጋፍ እና ቅንጅት አስፈላጊነት ላይ ሁለቱ ወገኖች መወያየታቸውን የአሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል።
የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሃሳን ሼክ ሞሃሙድ በበኩላቸው ጠንካራ እና የተረጋጋች ሶማሊያን ለመገንባት አሜሪካ በማሳየት ላይ ላለቸው ቀጣይነት ያለው ወታደራዊ እና ሲቪላዊ ትብብር አመስግነዋል።