በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አንጎላ ዛሬ እየመረጠች ነው


መራጮች ድምፅ እየሰጡ
መራጮች ድምፅ እየሰጡ
  • ለአንጎላ ምርጫ የአሜሪካ መልዕክት

ዛሬ በአንጎላ እየተካሄደ ላለው ምርጫ 26ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች ሲከፈቱ የሀገሪቱ ዜጎች ፕሬዚዳንታቸውን ጨምሮ አዲስ አመራር ይመርጣሉ።

ምርጫውን ለማሸነፍና መንግሥት ለመመስረት፣ በሥልጣን ላይ ያለው ገዢ ፓርቲ ለመጀመሪያ ግዜ ከተቃዋሚው ከፍተኛ ፉክክር ገጥሞታል።

የአሜሪካ ድምጹ ሞሃመድ ዩሱፍ እንደዘገበው፣ በትንሹ 14 ሚሊዮን አንጎላውያን ለምርጫ ሲመዘገቡ፣ ምርጫው በስልጣን ላይ ባሉትና የኤምፒኤልኤ ተወካይ ፕሬዚዳንት ጆአ ሎሬንሶ እና በተቀናቃኙ የዩኒታ መሪ አዳልቤርቶ ኮስታ መካከል ተቀራራቢ ፉክክር እንደሚካሄድ የፖለቲካ ታዛቢዎች በመናገር ላይ ናቸው።

220 የሚሆኑ የፓርላማ መቀመጫዎችም ለምርጫ ቀርበዋል።

የአንጎላ ድምፅ ሰጪዎች የአንድ ፓርቲ አገዛዝን በመቀጠልና፣ ከተቃዋሚው አዲስ ፕሬዚዳንትን በመምረጥ መካከል የመርጣሉ ብሏል የቪኦኤው ሞሃመድ ዩሱፍ ከናይሮቢ በላከው ዘገባ።

የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፣ የኢኮኖሚ ተግዳሮቶች በምርጫ ዘመቻው ዋና ጉዳይ ሆነው ባሉበት ወቅት፣ ተቃዋሚው ዩኒታ ወጣት ድምጽ ሰጪዎችን ሊስብ ችሏል። ከ 16 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አንጎላውያን በቀን ከ2 ዶላር በታች ገቢ ይኖራሉ።

ከሃገሪቱ ውጪ የሚኖሩ አንጎላውያን በዚህ ምርጫ ለመሳተፍ መብት ተሰጥቷቸዋል።

በአንጎላ ዛሬ የሚደረገው ምርጫ 5ኛው የብዝሃ-ፓርቲ ምርጫ ቢሆንም፣ ገዢው ኤምፒኤልኤ ሃገሪቱ ከፖርቹጋል ነጻ ከወጣችበት እአአ 1975 ጀምሮ በሥልጣን ላይ ከርሟል።

ዛሬ በአንጎላ በሚደረገው ምርጫ አስመልክቶ የአሜሪካው ኮንግረስ አባልና በውጪ ጉዳዮች የአፍሪካ፣ የዓለም ጤና እና ሰብዓዊ መብት ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ካረን ባስ ባስተላለፉት መልዕክት የትኛውም ፓርቲ ያሸንፍ፣ የዲሞክራሲ ሂደቱን መዋቅራዊ የሚያደርጉ ለውጦችን እንዲተገብር ጥሪ አድርገዋል።

ከካረን ባስ ቢሮ የተለቀቀው መግለጫ እንዳለው፣ አለም አቀፍ ታዛቢዎች የአንጎላን ምርጫ ለመታዘብ በመገኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን የገለጹት የካሊፎርኒያ የዲሞክራሲ ፓርቲ ወኪል የምክር ቤት አባሏ ካረን ባስ፣ የሃገሪቱ የምርጫ ኃላፊዎች የህዝብን ድምጽ አክብረው እንዲይዙ ጠይቀው ነጻ፣ ፍትሃዊ እና ግልጽነት ያለው ምርጫ እንዲሁም ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ለጠንካራ ዲሞክራሲ አስፈላጊ ናቸው ብለዋል።

አንጎላ እነዚህን የዲሞክራሲ መመሪያዎች እንደምትፈጽም ተስፋ አደርጋለሁ ያሉት የምክር ቤት አባሏ፣ ይህ ምርጫ በዩናይትድ ስቴትስና አንጎላ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከርና እንዲሁም የንግድና የጂኦፖለቲካ አዲስ ትብብር ለማድረግ በር የሚከፍት ጥሩ አጋጣሚ ነው ብለዋል።

“እንጎላውያን ድምጻቸው እንዲሰማ ጥረት በሚያደርጉበት በዚህ ወቅት፣ ዛሬ የሚደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ወሳኝ ክስተት ነው። አንጎላ በቀጠናው የኢኮኖሚ መሪ፣ ለአካባቢው ግጭቶች ገላጋይ፣ በቅርብ ዓመታት ደግሞ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር የጋራ ግንኝነቷን ያጠናከረች ሀገር በመሆኗ በተቃዋሚው አዳልበርቶ ኮስታ ጁኒየርና ለሁለተኛ ግዜ በሚወዳደሩት በተቀማጩ ፕሬዚዳንት ጆአ ሎሬንሶ መካከል የሚደረገው ፉክክርና ምርጫ ወሳኝ ነው” ያሉት ካረን ባስ አክለውም፤ “በተለይም ምርጫው ከአስቸጋሪውና በአፍሪካ ረጅም አገዛዞች ከነበረው የሆሴ ኤድዋርዶ ደኦስ ሳንቶስ አገዛዝ ወዲህ የሚደረግ በመሆኑ ወሳኝ ምርጫ ነው” ብለዋል ሲል ከጽህፈት ቤታቸው የወጣው መግለጫ አመልክቷል።

XS
SM
MD
LG