በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አሜሪካ የአፍጋኒስታንን ገንዘብ ወደ ስዊስ ማዛወሯን ታሊባን ተቃወመ


ፎቶ ፋይል - የታሊባን ዋና ቃል አቀባይ ዛቢሁላ ሙጃሂድ
ፎቶ ፋይል - የታሊባን ዋና ቃል አቀባይ ዛቢሁላ ሙጃሂድ

የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት በአሜሪካ ባክንኮች ተይዞ የነበረ 3.5 ቢሊዮን የአፍጋኒስታን ተቀማጭ ገንዘብን ስዊስ ወደሚገኝ ፈንድ ማሸጋገሩን ታሊባን ዛሬ አውግዟል።

የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት በአሜሪካ ባክንኮች ተይዞ ከነበረው የአፍጋኒስታን ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ 3.5 ቢሊዮን ዶላር በመጠቀም “የአፍጋኒስታንን ኢኮኖሚ ለማረጋጋት” በሚል በስዊዘርላንድ ፈንድ ማቋቋሙን ከትናንት በስቲያ አስታውቆ ነበር። በዚህ ፈንድ ላይ ግን ገዢው ታሊባን ምንም ሥልጣን እንዳልተሰተው ታውቋል።

የቪኦኤው አያዝ ጉል ከካቡል እንደዘገበው የታሊባን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤት ዕቅዱን “ተቀባይነት የሌለው” ሲል አጣጥሎ “ከዓለም አቀፍ መርኆች ያፈነገጠ ነው” ሲል ገልጾታል።

በታሊባን የሚመራው የአፍጋኒስታን መንግሥት በአሜሪካ ባንኮች የሚገኝና በዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት የታገደ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ተቀማጭ ገንዘብ እንዲመለስለት ሲወተውት የቆየ ሲሆን በዛሬው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤት መግለጫም አሜሪካ ገንዘቡን እንድትለቅ እንዲሁም የአፍጋን ነጋዴዎች የዓለም አቀፍ ባንኮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻልና በድህነት የተመታቸውን ሃገር ለመታደግ እንዲቻል ተጥለው የነበሩ የገንዘብ ማዕቀቦችን እንድታነሳ በድጋሚ ጠይቋል።

“የአፍጋናውያንን ጥያቄ ችላ በማለት ገንዘቡ የሚለቀቅ ከሆነ የአፍጋኒስታን እስላማዊ ኤምሬት ይህን ገንዘብ በመጠቀም እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ግለሰቦች፣ ተቋማትና የንግድ ድርጅትችን ለመቅጣት ይገደዳል” ሲል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ስታውቋል።

ከአንድ ዓመት በፊት አፍጋኒስታንን የተቆጣጠረውና በወንዶች ብቻ የተቋቋመው የታሊባን መንግሥት ሃገሪቱን “እስላማዊ ኤምሬት” ብሎ ይጠራታል። ቀሪው ዓለም ግን የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይና የአሸባሪዎች እንቅስቃሴ አሳሳቢ በመሆኑ እውቅና አልሰጠውም።

ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ታሊባን አፍጋኒስታንን ሲቆጣጠርና ዓለም አቀፍ ድጋፍ የነበረው የካቡል መንግሥት ሰራዊት ሲበተን እንዲሁም የአሜሪካንና የኔቶ ጦሮች ሃገሪቱን ለቀው ሲወጡ በኒው ዮርክ ተቀማጭ የነበረን 7 ቢሊዮን ዶላር የአፍጋኒስታን ገንዘብ ዩናይትድ ስቴትስ አግዳለች።

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከዚህ ገንዘብ ግማሹን፣ ማለትም 3.5 ቢሊዮን ዶላሩን ለተቋቋመው የአፍጋን ፈንድ እንዲለቀቅ፣ ቀሪው ደግሞ ከሃያ ዓመታት በፊት በአሜሪካ ላይ በተፈጸመው የሽብር ጥቃት ተጎጂ ለሆኑ ሰዎች እንዲውል ባለፈው የካቲት ትዕዛዝ ሰትተዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ግምጃ ቤት እንዳስታወቀው በስዊዘርላንድ የተቋቋመውና በባላደራዎች ቦርድ የሚተዳደረው ፈንድ፣ የአፍጋኒስታንን ሃብት ለመጠበቅና ግንዘቡ ለታለሙ ጉዳዮች እንዲውል ለማድረግ ያለመ ነው።

ገንዘቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማስገባት ለዓለም አቀፍ ተቋማት ዕዳ ክፍያ እና አፍጋኒስታን ለልማት ዕርዳታ ብቁ እንድትሆን ዋስትና የሚውል ነው ተብሏል።

XS
SM
MD
LG