በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በመሪዎቹ ላይ የተጣለው የጉዞ እገዳ እንዲነሳ ታሊባን ጠየቀ


ፎቶ ፋይል፦ በኳታር የሚገኘውን የታሊባን የፖለቲካ ቢሮ የሚመሩት ሱሄል ሻሂን እአአ 5/28/2019
ፎቶ ፋይል፦ በኳታር የሚገኘውን የታሊባን የፖለቲካ ቢሮ የሚመሩት ሱሄል ሻሂን እአአ 5/28/2019

የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ለማሳለጥ እንዲቻል በመሪዎቼ ላይ የተጣለው የጉዞ እገዳ ይነሳልኝ ሲል ታሊባን ጠየቀ። የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት እገዳውን በማንሳት በጉዳይ ላይ ለሁለት ተከፍሏል።

የፀጥታው ም/ቤት አባላት ለታሊባን መሪዎች የተሰጠውን ግዜያዊ የጉዞ ፈቃድ ለማራዘም ባለመስማማታቸው፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩን አሚር ካን ሙታቂን ጨምሮ ለ13 የታሊባን መሪዎች የተሰጠው ፈቃድ ባለፈው ዓርብ መቃጠሉን የቪኦኤው አያዝ ጉል ከኢስላማባድ የላከው ዘገባ አመልክቷል።

“የጉዞ እገዳው ለውይይትና ለግንኙት በር የመዝጋትን ያህል ይቆጠራል፤ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ለሚደርግ ጥረት እንቅፋት” ነው ሲሉ በኳታር የሚገኘውን የታሊባን የፖለቲካ ቢሮ የሚመሩት ሱሄል ሻሂን ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

በእአአ 2011 በወጣው የፀጥታው ም/ቤት ውሳኔ መሰረት በድምሩ 135 የሚሆኑ የታሊባን ባለሥልጣናት የሃብትና የጉዞ እገዳዎችን የሚጨምር ጠቅላላ ማእቀብ ተጥሎባቸዋል።

ጊዜያዊ ፈቃድ ሲሰጣቸው የቆዩት 13 ባለሥልጣናት፣ ከም/ቤቱና ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ፣ ከሌሎች ሃገራት ባለሥልጣናት ጋር ለሚያደርጉት የሰላም ንግግር ጉዞ ማድረግ እንዲችሉ ታስቦ የተፈጸመ ነበር።

በአብዛኛው የአፍጋኒስታን ክፍል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ለሴቶች መከልከሉን በመቃወም፣ የፀጥታው ም/ቤት የአፍጋኒስታን ማዕቀብ ኮሚቴ ለሁለት የሃገሪቱ የትምህርት ሚኒስትሮች ተሰጥቶ የነበረውን ግዜያዊ የጉዞ ፈቃድ ባለፈው ሰኔ መሰረዙን የአያዝ ጉል ዘገባ ጨምሮ አመልክቷል።

ባለፈው ወር የአልቃይዳው መሪ አይመን አል-ዛዊሂሪን በካቡል እምብርት በሚገኘው ቤቱ እያለ በድሮን መትታ መግደሏን ዩናይትድ ስቴትስ አስታውቃለች። የአል-ዛዊሂሪ በዛ መገኘት ታሊባን በፀረ-ሽብር ላይ የገባውን ቃል ስለማክበሩ ጥያቄ አስነስቷል።

XS
SM
MD
LG