በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ታሊባን የመጨረሻውን አሜሪካዊ ታጋች ለቀቀች


ባሽር ኑርዛይ
ባሽር ኑርዛይ

ታሊባን የመጨረሻውን አሜሪካዊ ታጋች ዛሬ ሰኞ በእስረኛ ልውውጥ ለቃለች።

ከሁለት ዓመት በፊት ካቡል ውስጥ ተጠልፎ የነበረውና 60 ዓመት የሚጠጋው መሃንዲስና የባህር ኃይል አባል ማርክ ፍሬሪክስ የተለቀቀው ባሽር ኑርዛይ በተባለ የታሊባን አባልና የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪ አለቃ ምትክ ነው።

አሜሪካና የኔቶ አጋሮቿ በወቅቱ በምዕራቡ ዓለም ይደገፍ ከነበረው የአፍጋን መንግሥት ጎን በመቆም የታሊባን አማጺያንን በመፋለም ላይ በነበሩበት ወቅት ነው ፍሬሪክስ ተይዞ የነበረው።

ባሽር ኑርዛይ፣ ሃጂ ባሽር በሚባል ተጨማሪ ስም የሚታወቅ ሲሆን በሚሊዮን ዶላር የሚገመት ሄሮይን ወደ አሜሪካ በማስገባቱ ከ17 ዓመታት በፊት ኒው ዮርክ ውስጥ ተይዞ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት ነበር። ባሽር ኑርዛይ ከአደንዛዥ ዕጽ ሽያጩ በሚያገኘው ገቢ ታሊባንን በገንዘብ ይደግፍ ነበር ተብሏል።

የኑርዛይ ጠበቃ ግን ደንበኛቸው የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪ አለቃ መሆኑን በመካድ፣ የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንደማይያዝ ነግረው አታለውት እንደይዙትና ክሱም ውድቅ መደረግ እንዳለበት ተናግረዋል።

የታሊባን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አሚር ካን ሙታቂ በመንግሥታቸውና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል የእስረኛ ልውውጡ የተካሄደው በአፍጋን መዲና በሚገኘው የአየር ማረፊያ መሆኑን ለዜና ሰዎች ተናግረዋል ሲል የቪኦኤው አያዝ ጉል ከኢስላማባድ ዘግቧል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለው እንዳሉት የእስረኛ ልውውጡ የተካሄደበት ሁኔታ “ከዚህ በፊት በአፍጋኒስታን ታሪክ ተደርጎ በማያውቅ” ሁኔታ የተፈፀመ ሲሆን፣ በታሊባንና በአሜሪካ መካከል በተደረገና ረጅም ግዜ ከወሰደ ድርድር በኋላ የተፈጸመ ነው። በታሊባንና በአሜሪካ መካከል እስከ አሁን የእስረኞች ልውውጥ ይካሄድ የነበረው ከአፍጋኒስታን ውጪ እንደነበር ሚኒስትሩ አክለው ገልጸዋል።

ኑርዛይ ተጽእኖ ማድረግ የሚችል የጉሳ መሪ ሲሆን፣ በደቡብ ካንዳሃር አውራጃ የኦፒዩም አደንዛዥ ዕጽ እርሻ ነበረው። የታሊባን መስራችና መሪ የነበረው ሙላ ሞሃመድ ኦማር የቅርብ አጋር እንደነበርም ታውቋል።

XS
SM
MD
LG