በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሠራተኛ ማኅበራት ኮንፈዴሬሽን የመቶ ሺሕዎች ሰላማዊ ሰልፍ መከልከሉ ተገለጸ


አዲስ አበባ ከተማ
አዲስ አበባ ከተማ

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፈዴሬሽን፣ የዓለም ላብ አደሮችን ቀን ምክንያት በማድረግ፣ በዐዲስ አበባ ሊያደርግ ያቀደው ሰላማዊ ሰልፍ፣ በከተማዋ የሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ መከልከሉን አስታወቀ፡፡

የኮንፈዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ፣ ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት፣ በታቀደው ሰላማዊ ሰልፍ፥ የሠራተኞችን ልዩ ልዩ ጥያቄዎች ለመንግሥት ለማቅረብ አስበው እንደነበር አመልክተዋል፡፡ ኾኖም፣ ወደ አደባባይ የምትወጡት፣ የዓለም ላብ አደሮችን ቀን ለማክበር ሳይኾን፣ ሌላ ጥያቄ ለማሰማት ነው፤ በሚል፣ ሰልፉን እንዳያደርጉ መከልከላቸውን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፈዴሬሽን፣ በየዓመቱ ሚያዝያ 23 ቀን የሚከበረውን የዓለም ላብ አደሮች ቀን፣ በሰላማዊ ሰልፍ ለማክበር ዐቅዶ እንደነበር አስታውቋል፡፡ በዚኽ ሰልፍ፣ የሠራተኛውን የተለያዩ ጥያቄዎች ለመንግሥት ለማቅረብ ታስቦ እንደነበር፣ የኮንፈዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ፣ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ገልጸዋል፡፡

በዚኽ ሰላማዊ ሰልፍ፣ ከአሠሪ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ጋራ በተያያዘ የወጣው 20/80 በሚል የሚታወቀው መመሪያ፣ በፍጥነት ተግባር ላይ ይዋል፤ የሚል ጥያቄ ለማቅረብ አስበን ነበር፤ ብለዋል ፕሬዚዳንቱ፡፡

ማንኛውም ኤጀንሲ፣ ለድርጅቶች ሠራተኞችን ሲያቀርብ፣ ኤጀንሲው፣ ከቀጣሪው ድርጅት ከሚያገኘው ገቢ 20 በመቶ ለራሱ፣ 80 በመቶ ደግሞ ለሠራተኛው እንዲሰጥ መመሪያው ያስገድዳል፡፡ አሁን ግን በመመሪያ መሠረት እየተፈጸመ አለመኾኑን ገልጸዋል፡፡ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ፣ መንግሥት ግጭቶችን በሰላም ለመፍታት እያደረገው ላለው ጥረትም ድጋፋችንን ለመግለጽ ዐቅደን ነበር፤ ያሉት አቶ ካሳሁን ፎሎ፣ ኾኖም ሰልፉ፣ በዐዲስ አበባ የሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ መከልከሉን ተናግረዋል፡፡

በመስቀል አደባባይ ሊደረግ ታስቦ በነበረው ሰልፍ ላይ፣ እስከ 100ሺሕ ሠራተኞች ይሳተፋሉ፤ የሚል ግምት እንደነበር የጠቀሱት አቶ ካሳሁን፣ የጸጥታውን ኹኔታ ለመጠበቅ፣ አራት ሺሕ አስተባባሪዎች

ተዘጋጅተው እንደነበር አመልክተዋል፡፡ በዚኽ ጉዳይ ላይ፣ የዐዲስ አበባ ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮን አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡

የዐዲስ አበባ ፖሊስ በበኩሉ፣ በዛሬው ዕለት በከተማዋ፣ የላብ አደሮችን ቀን አስመልክቶ የሚደረግ ምንም ዐይነት የአደባባይ ሰልፍ እንደማይኖር በትላንትናው ዕለት አስታውቆ ነበር፡፡

XS
SM
MD
LG