ተዘግተው የነበሩት ሆቴሎች እንዲከፈቱ የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማኅበር ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ያስታወቁት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ አስቴር ሰለሞን፣ አሁን ላይ ሁሉም ሆቴሎች ተከፍተው ወደ ሥራ መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡
ለወራት ተዘግተው ከቆዩ በኋላ የተከፈቱ ሆቴሎች ለተለያየ ኪሳራ መዳረጋቸውን ገልጸው ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል። ደንቦችን በመተላለፍ፣ ህወሓትን በመደገፍ እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊትን በሚያዋርዱ ተግባራት ላይ ተሰማርተዋል በሚል ተጠርጥረው፣ ለረዥም ጊዜ ተዘግተው የቆዩ ሆቴሎች፣ በአሁኑ ወቅት ተከፍተው ወደ ሥራ መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡
ከነዚህ ሆቴሎች መካከል የሆነው የሆሊዴይ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ ፈቃዱ አብርሃም፣ ሆቴሉ ከስምንት ወራት በኋላ መከፈቱን ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።
የካሌብ ሆቴል ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጌታብቻ ደጀኔም እንዲሁ ሆቴላቸው ወደ ሥራ መመለሱን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከመንግሥት አካል መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ሆቴሎቹ በተዘጉበት ወቅት ድርጊቱ ማንነትን ማዕከል ያደረገ እንደሆነ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ቢገልጹም፣ መንግሥት ውንጀላውን ማስተባበሉ አይዘነጋም።