የዩናይትድ ስቴትስ እና የዩክሬን ባለስልጣናት ማክሰኞ በሳዑዲ አረብያ፣ ጅዳ ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ፣ የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በዩክሬን የስለላ መረጃ ማጋራት ላይ ጥሎት የነበረውን እገዳ እንደሚያነሳ እና ለዩክሬን የፀጥታ ድጋፍ መስጠት እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ ባለስልጣናት በሚቀጥሉት ቀናት ከሩሲያ ባለስልጣናት ጋር እንደሚነጋገሩ ይጠበቃል። የትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮቭ በዚህ ሳምንት ከሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በሞስኮ ይገናኛሉ ተብሏል።
ስምንት ሰዓት ከፈጀ ንግግር በኃላ ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በምታካሂደው ጦርነት "አስቸኳይ የ30-ቀናት ተኩስ አቁም" ለማድረግ ዩናይትድ ስቴትስ ያቀረበችውን ሃሳብ ለመቀበል ዝግጁ መሆኗን ያስታወቀች ሲሆን፣ ክሬምሊንም ሀሳቡን መቀበል ይኖርበታል።
የካቲት 26፣ 2017 ዓ.ም ትራምፕ ከዩክሬን ጋር ይደረግ የነበረውን የስለላ መረጃ ልውውጥ እንዲቋረጥ ያዘዙት፣ የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮለድሚር ዘለንስኪ ጦርነቱን ለማቆም ከሩሲያ ጋር እንዲነጋገሩ ግፊት ለማድረግ መሆኑ ተመልክቷል።
ክሬምሊን ዩናይትድ ስቴትስ እና ዩክሬን ባቀረቡት የተኩስ አቁም ሀሳብ ዙሪያ እስካሁን ምንም አስተያየት አልሰጠም። ሆኖም የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት፣ በዚህ ሳምንት ከዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት ጋር ድርድር ሊደረግ እንደሚችል አመልክቷል።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እና የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ማይክ ዋልትዝ በጅዳ በተካሄደው ውይይት ላይ የተሳተፈውን የአሜሪካ ልዑካን ቡድን የመሩ ሲሆን ዘለንስኪ በስብሰባው ላይ አልተገኙም። በምትካቸው የዘለንስኪ ዋና አማካሪ አንድሪይ የርማክ፣ የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሪ ሺቢሃ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ ሩስቴም ኡሜሮቭ እና የጦር አዛዥ ኮማንደር ፓቭሎ ፓሊሳ ተገኝተዋል።
ከውይይቱ በኃላ ሩቢያ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል ዩክሬን ጦርነቱን ለማስቆም የሚያስችል አንድ እርምጃ ወደፊት ተራምዳለች ብለዋል። "አሁን ይህንን ሀሳብ ወደ ሩሲያኖች እንወስዳለን። እናም እንደሚስማሙ ተስፋ እናደርጋለን። ለሰላም ሲሉ ይስማማሉ። አሁን ኳሱ በእነሱ ደጅ ነው ያለው" ብለዋል።
መድረክ / ፎረም