የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ፍራንሲስ በፋሲካ ጾም ወቅት የሚደረገውን የቤተ ክርስቲያኒቱን ጉባኤ ሮም ከሚገኘው ሆስፒታል በርቀት በመከታተል ላይ መኾናቸው ታውቋል።
ከገጠማቸው የሳምባ ምች በማገገም ላይ ያሉት አባ ፍራንሲስ ከሆስፒታል አልጋቸው ላይ ሆነው ጉባኤውን በቪዲዮ በመከታተል ላይ ሲኾኑ፣ የጉባኤው ተሳታፊዎች ግን እርሳቸውን ማየትም ሆነ መስማት እንደማይችሉ የአሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል።
የአንድ ሳምንቱ ጉባኤ፣ እስከ ፋሲካ የሚቆየው የቤተ ክርስቲያኗ ዐብይ ጾም በሚጀምርበት ወቅት በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን፣ አባ ፍራንሲስም በርቀት ከሌሎቹ የቤተክርስቲያኗ ጳጳሳት ጋራ በጉባኤው እንደሚሳተፉ ቫቲካን አስታውቃለች፡፡
ለ12 ዓመታት ሊቃነ ጳጳስነት የቆዩት አባ ፍራንሲስ በሕመም መያዛቸው ቀጣዩ የጵጵስና ዘመናቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ጥያቄ ጭሯል።
የሳምባ ምቹ ተባብሶ ሁለቱም ሳምባዎችና የመተንፈሻ ቧንቧቸውም ለመቆጣት እንደበቃ ታውቋል። ባለፈው አንድ ሳምንት ግን በተረጋጋ ሁኔታ እንደሚገኙ እንዲሁም ትኩሳትና የኦክሲጅን መጠን መወላወል እንዳልገጠማቸውም ታውቋል። እንዲህ ዐይነቱ መሻሻል ጳጳሱ የሚሰጣቸው ሕክምና እየሠራ ለመሆኑ አመልካች እንደሆነ ሐኪሞቻቸው አስታውቀዋል።
የአባ ፍራንሲስ ባእለ ሲመት ሐሙስ የሚከበር ሲሆን፣ ይህም ለመጀመሪያ ጊዜ የማይታደሙበት እንደሆነ ታውቋል።
በትላንትናው ዕለት እሑድ፣ አባ ፍራንሲስ ከከፍተኛ የቤተ ክርስቲያኒቱ ኅላፊዎችና ጳጳሳት ጋራ በሆስፒታል ሳሉ ለሦስተኛ ጊዜ እንደተገናኙ የአሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል።
አባ ፍራንሲስ ከእርሳቸው በፊት የነበሩት አባ ቤኔዲክት በፈቃዳቸው ቦታውን በመልቀቃቸው ቢያደንቁም፣ የሊቃነ ጳጳሳት ቦታው የሕይወት ዘመን መሆኑንና ለመልቀቅም ሐሳብ እደሌላቸው በቅርቡ አስታውቀዋል።
መድረክ / ፎረም