ትላንት የመተንፈስ ችግር አጋጥሟቸው የነበሩት የሮማ ካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ አባ ፍራንሲስ፣ ሌሊቱን በሰላም ተኝተው ማደራቸውን የቫቲካን ባለሥልጣናት ገለጹ። "ዛሬ ቡናቸውን ጠጥተዋል፣ ጋዜጣም አንብበዋል" ብለዋል።
ሮም የሚገኘው ጄሜሊ ሆስፒታል ከገቡ ሁለት ሳምንት የሆናቸው የ88 ዓመቱ አባ ፍራንሲስ፣ ትላንት ከመተንፈስ ጋራ የተያያዘ እክል ገጥሟቸው በሚያስመልሱበት ወቅት ትንፋሽ ሲወስዱ ትንታ አብሮ ገብቶ የመተንፈስ ችግር አጋጥሟቸው ነበር።
ከዚኽ እክል በኋላም፣ ለመተንፈስ በሚረዳ መሣሪያ ሕክምና እንደተደረገላቸው የቫቲካን መግለጫው አውስቷል። የሕክምና ርዳታው ሲደረግላቸው ንቁ ሆነው ከሀኪሞቻቸው ጋራ እየተባበሩ እንደነበር ባለሥልጣናቱ አክለዋል።
የትላንቱ ችግር ከመከሰቱ አስቀድሞ አባ ፍራንሲስ ላለፉት ሦስት ቀናት ከህመማቸው እያገገሙ መኾኑ ሲገለጽ ነበር።
አባ ፍራንሲስ በሚቀጥለው ሳምንት የአርባ ጾም መቀበያ ቅዳሴን እንደማይመሩ ትላንት ከቫቲካን የተሰጠው መግለጫ አመልክቷል።
መድረክ / ፎረም