በግሪክ በርካታ ሰዎችን ለሞት የዳረገውን የባቡር አደጋ ሁለተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተቃውሞ ሰልፎችን ያካሄዱ ሲኾን፣ የባቡር፣ የአየር እና የባህር ትራንስፖርት ሠራተኞችም የሥራ ማቆም አድማ አድርገዋል።
በማዕከላዊ ግሪክ ተማሪዎችን የጫነ የመንገደኞች ባቡር ከዕቃ ጫኝ ባቡር ጋራ ተጋጭቶ የ57 ሰዎች ሕይወት ያለፈው እንደ አውሮፓውያን የቀን አቆጣጠር በየካቲት 28 ቀን 2023 ነበር።
አደጋው ከደረሰ ከሁለት ዓመት በኋላ ለአደጋው መንስዔ የነበሩ የደኅንነት ክፍተቶች ያልተሟሉ መኾኑን ሐሙስ ዕለት ይፋ የተደረገ ምርመራ አመልክቷል።
በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገ ሲኾን፣ በአደጋው እስካሁን ማንም ተጠያቂ አልሆነም።
በዚህም ምክንያት በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ በደርዘን የሞቆጠሩ ከተሞች የተጠራውን ሕዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች፣ የባህር ትራንስፖርት ሠራተኞች፣ የባቡር ሹፌሮች፣ ዶክተሮች፣ ጠበቆች እና አስተማሪዎች የተቀላቀሉ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ በራዎች እንዲቆሙ ተደርገዋል። የንግድ ቤቶች እና ቲያትር ቤቶችም መዘጋታቸው ታውቋል።
እ.አ.አ በ2023 ከደረሰው አደጋ በኋላ በድጋሚ ምርጫ አሸንፈው ለዘብተኛ ቀኝ ዘመም መንግሥት የመሰረቱት ጠቅላይ ምኒስትር ኪሪያኮስ ሚትሶታኪስ፣ ፖለቲካዊ ኃላፊነት መውሰድ የሚያስችል ጥያቄ በፓርላማ ባለማንሳታቸው በተጎጂዎቹ ቤተሰቦ ተደጋጋሚ ትችት ይቀርብባቸዋል።
በአደጋው እጁ እንደሌለበት የሚገልጸው መንግሥት በበኩሉ፣ የአደጋውን መንስዔ የማጣራት የፍትህ አካል ሥራ መሆኑን ገልጿል።
መድረክ / ፎረም