የሮማ ካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ አባ ፍራንሲስ ጤናቸው በአስጊ ሁኔታ ላይ ቢሆንም ትንሽ መሻሻል እንዳሳዩ ቫቲካን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የ88 ዓመቱ ሊቀ ጳጳስ አባ ፍራንሲስ በመተንፈሻ አካል ሕመም እና ሌሎች ተያያዥ የጤና ችግሮች ምክንያት፣ እ.አ.አ ከየካቲት 14 ጀምሮ ሮም የሚገኘው ጄሜሊ ሆስፒታል ውስጥ ህክምና እየተደረገላቸው ይገኛሉ።
ማክሰኞ ዕለት በቅዱስ ጳውሎስ አደባባይ የተገኙ አማኞች እና ጎብኚዎች ግን በአባ ፍርንሲስ የጤና ሁኔታ መጨነቃቸውን እና ተስፋቸውን ገልጸዋል።
ከፖላንድ የመጡ ቄስ አባ አርተር ፣ "ስለኛ መልካም የሚያስቡ አባታችን ናቸው። ሁላችንንም ልክ ስለወላጆቻችን እንደምንጨነቀው ሁሉ ያሳስበናል። ስለአባታችን ተጨንቀናል። ስለዚህ እንዲሻላቸው እንፈልጋለን። ነገር ግን ሁሉም በእግዚአብሔር እጅ ነው።" ብለዋል።
ሊቀ ጳጳሱ ያጋጠማቸው ኢንፌክሽን ውስብስብ መሆኑን እና በሁለት እና ከዛ በላይ በሆኑ ረቂቅ ተሕዋያን አማካኝነት የተከሰተ መሆኑን የቫቲካን መግለጫ አመልክቷል።
ተደራራቢ የሳምባ ምች በሽታ በሁለቱም ሳንባዎች ላይ ጠባሳ ሊያስከትል የሚችል ከባድ በሽታ ሲሆን፣ ለመተንፈስ አዳጋች ይሆናል።
እ.አ.አ ከ2013 ጀምሮ በሮማ ሊቀ ጳጳስነት እያገለገሉ የሚገኙት አባ ፍራንሲስ ያለፉትን ሁለት ዓመታት በተለያዩ የጤና እክሎች ሲሰቃዩ ቆይተዋል።
በተለይ በልጅነታቸው ባጋጠማቸው ሕመም ምክንያት የአንዱን ሳምባቸውን ግማሹን ክፍል በማጣታቸው፣ በቀላሉ ለሳምባ ኢንፌክሽን በሽታዎች እንደሚጋለጡ ተመልክቷል።
መድረክ / ፎረም