የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕና የሩሲያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን ፊት ለፊት የሚገናኙበት ስብሰባ ዝግጅት መጀመሩን የሩሲያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታውቀዋል፡፡ ይህም በዩክሬን ጦርነት ምክንያት በምዕራባውያን ለተገለለቸው ሩስያ ትልቅ ለውጥን የሚያመጣላት ነው ተብሏል፡፡
ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ሰርጌይ ራያብኮቭ ለሃገራቸው የመንግስት መገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት የፑቲንና ትራምፕ የመሪዎች ስብሰባ በዩክሬን ያለውን ጦርነት ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ ጉዳዮች ላይም ያተኮሩ ሰፊ ውይይትን ያካተተ ይሆናል ብለዋል፡፡
ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱን ስብሰባ ለማደራጀት ጥረቶች ገና ጅምር ላይ ናቸው ፣ እናም ይህንን ለማድረግ “በጣም የተጠናከረ የቅድመ ዝግጅት ሥራን ይጠይቃል” ብለዋል ።
ሪያብኮቭ አክለውም የዩናይትድናይትድ ስቴትስና የሩሲያ ልዑካን በከፍተኛ ባለስልጣናት መካከል ለቀጣይ ንግግሮች መንገድ ለመክፈት "በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ" ሊገናኙ እንደሚችሉም ጠቁመዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት ተወካዮች ማክሰኞ እለት በሳኡዲ አርቢያ በዩክሬን ያለውን ጦርነት ለማስቆምና ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል ተስማምተዋል ።
በስብሰባው ላይ የዩክሬን ልዑክ ያልተሳተፈ ሲሆን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ኪየቭ ባልተሳተፈችበት የውይይቱ ምንም አይነት ውጤት ሀገራቸው እንደማትቀበል ገልጸው ባለፈው ረቡዕ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሊያደርጉ የነበረውን ጉዞም አራዝመዋል።
መድረክ / ፎረም