ከአሜሪካ የተባረሩትን ፍልሰተኞችን በጊዜያዊነት ለማስተናገድ ኮስታሪካና ሆንዱራስ ከፓናማ ጋራ ተቀላቀለዋል፡፡
በዐዲሱ የትረምፕ አስተዳደር የኢምግሬሽን ፖሊሲ ከሀገር የተባረሩና የተለያየ ሀገር ዜግነት ያላቸው 135 ስደተኞችን የጫነ አውሮፕላን ትላንት ሐሙስ ኮስታሪካ ዋና ከተማ አርፏል፡፡
65 ህፃናት ይገኙበታል የተባሉት እነዚህ ፍልሰተኞች ከኡዝቤክስታን፣ ከቻይና ከአፍጋኒስታን ከሩሲያ እና ከሌሎች ሀገሮች የመጡ ናቸው፡፡ፍልሰተኞቹ ወደ የሀገራቸው ከመሸኘታቸው በፊት ኮስታሪካ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋራ በገባችው ስምምነት መሰረት በሀገሯ ታቆያለች፡፡
ኮስትሪካ፣ ፓናማ እና ሆንዱራስ ወደ ሌሎች ሀገሮች የሚላኩ ፍልሰተኞችን ለጊዜው ተቀብለው ለማቆየት ከዩናይትድ ስቴትስት ጋራ ስምምነት የተፈራረሙ ሀገሮች ናቸው፡፡
ፓናማ በቅርቡ በመጀመሪያው ዙር የተላኩ 299 ፍልሰተኞችን የተቀበለች ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑት በሆቴል ክፍሎች ውስጥ ሲቀመጡ ሌሎች ደግሞ በኮሎምቢያ ድንበር አቅራቢያ ወደሚገኝና ራቅ ወዳለ ካምፕ ተልከዋል፡፡
ሆንዱራስ በአሜሪካና በቪንዙዌላ መካከል ቀጥተኛ በረራ ባለመኖሩ “የሰብአዊ ድልድይ” ብላ በጠራቸው የማጓጓዝ አገልግሎት 170 ቬንዙዌላውያንን ከጓንታናሞ ቤይ ወደ ቬንዙዌላ በማዛወር ረድታለች፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በቅርቡ ባደረጉት ጉብኝት ከሀገራቱ ጋራ በተደረሰው ስምምነት ዩናይትድ ስቴትስ የመጓጓዣውንና የማቆያውን ሙሉ ወጪዎች ትሸፍናለች፡፡
ፕሬዚዳንት ትረምፕ የደቡብ አሜሪካ ሀገራት ህገወጥ ስደተኞችን በመግታት፣ በመቀበል ወይም ሁኔታዎችን በማመቻችት እንዲተባበሩ ጫና አሳድረዋል፡፡
ከተባበረሩት ፍልሰተኞች መካከል በተለይም ከእስያ የመጡት ወደ የሀገራቸው ከመመለሳቸው በፊት እስከ ስድስት ሳምንታት ሊቆዩ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡
ስደተኞች ወደ ሀገራቸው፣ ካልሆነም በተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የፍስልተኞች ድርጅት አማካይነት፣ ወደ ሌላ ተቀባይ ሀገር የመሄድና የጥገኝነት መብታቸው ሊጠበቅ የሚችልበት አግባብ እንደሚኖር የኮስታሪካ ባለሥልጣናት ተናግረዋል፡፡
መድረክ / ፎረም