ቻድ በቦኮ ሃራም ነውጠኞች ላይ ለአራት ወራት ባደረገችው ዘመቻ 300 የሚጠጉ አባላቱን መግደሏን አስታውቀች፡፡ ትላንት ማክሰኞ መጠናቀቁ በተገለጸው ዘመቻ 27 የቻድ ሠራዊት አባላት ሕይወታቸውን ማጣታቸውም ታውቋል፡፡
ባለፈው ጥቅምት ቦኮ ሃራም 40 የቻድ ጦር አባላትን በካምፓቸው ሳሉ ጥቃት በማድረስ መግደሉን ተከትሎ ነበር የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ማሃማት ኢድሪስ ዴቢ ኢንቶ በቡድኑ ላይ ወታደራዊ ዘመቻ እንዲካሄድ ትዕዛዝ የሰጡት፡፡
በናይጄሪያ የነበረው ቦኮ ሃራም ባለፉት ዐሥር ዓመታት በቻድ ሃይቅ አካባቢ ወዳሉ ሃገራት፣ ማለትም ቻድ፣ ካሜሩንና ኒዤር በመሰራጨቱ፣ ቻድ በቀጠናው ቦኮ ሃራምና አጋሮቹን ከሚፋለሙ አራት ሃገራት አንዷ ሆናለች፡፡ በአራቱ ሃገራት 40 ሺሕ የሚሆኑ ሰዎች በግጭቱ ሕይወታቸውን እንዳጡ ይነገራል።
ቻድ ከቀድሞ ቅኝ ገዢዋ ፈረንሣይ ጋራ ያላትን ግንኙነት አቋርጣ ጦሯ ከሀገሯ እንዲወጡ አድርጋለች፡፡
የቱርክ ወታደራዊ አሠልጣኞች በያዝነው ወር ቻድ ገብተው፣ ከቱርክ የተገዙ ድሮኖችን አጠቃቀም ሥልጠና በመስጠት ላይ መኾናቸውን ወታደራዊ ምንጮች እንዳስታወቁ የኤኤፍፒ ዜና ወኪል ከላከው ሪፖርት መረዳት ተችሏል።
መድረክ / ፎረም