የእስራኤል ወታደሮች ከታጣቂው ሄዝቦላህ ጋራ በተደረሰበት የተኩስ አቁም ስምምነት መሰረት፣ አካባቢውን ለቀው መውጣት በሚገባቸው የዛሬው ማክሰኞ ቀነ ገደብ ከአንዳንድ የደቡብ ሊባኖስ አካባቢዎች ለቀው አለመውጣታቸው ተነገረ፡፡
እስራኤል በክልሉ ከሚገኙ አንዳንድ መንደሮች ለቃ ብትወጣም፣ የሰሜናዊ እስራኤልን የተወሰኑ ክፍሎችን ለመጠበቅ አስፈላጊ ናቸው ካለቻቸው አምስት ቦታዎች ኃይሏን ያላስወጣች መሆኑን ተናግራለች።
የሊባኖስ ፕሬዝደንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የፓርላማ አፈ-ጉባኤ ዛሬ ማክሰኞ በሰጡት የጋራ መግለጫ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት እስራኤል በአስቸኳይ እንድትወጣ እንዲጠይቅ ጥሪ አቅርበዋል።
መግለጫው "በማንኛውም ስንዝር የሊባኖስ ግዛት ውስጥ የእስራኤል ጦር መገኘት ወረራ ነው፣ በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት የሚያስከትላቸው መዘዞች አሉት" ሲል ገልጿል።
የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሂዝቦላህ ከእስራኤል ድንበር ርቆ እንዲሄድ እና የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ኃይሎች ከሊባኖስ ወታደሮች ጋራ በተለቀቀው የመከላከያ ቀጠና እንዲሰማሩ ከማድረግ ጋራ፣ እስራኤል በጥር መጨረሻ ለቃ እንድትወጣ ይጠይቃል፡፡ የተራዘመው ቀነ-ገደብ ወደ ዛሬ ማክሰኞ እንዲገፋ መደረጉም ተመልክቷል፡፡ ፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የሊባኖስ ተወካይ ጄኒን ሄኒስ-ፕላስቻርት እና በሊባኖስ የተባበሩት መንግሥታት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አሮልዶ ላዛሮ በጋራ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተግባራዊ የሚደረግበት ሌላ የተራዘመ ቀን መኖሩ “እኛ ይሆናል ብለን ያሰብነው አይደለም” ብለዋል።
መግለጫው አክሎም "ሁለቱም ወገኖች ግዴታቸውን እንዲወጡ እንጠይቃለን። በመንደሮቻቸው እና በከተሞቻቸው ላይ እየደረሰ ካለው መጠነ ሰፊ ውድመት ጋር የሚታገሉት የደቡብ ሊባኖስ ማህበረሰቦች፣ እንዲሁም ቤታቸውን ለቀው ለመውጣት የተገደዱት የሰሜን እስራኤል ነዋሪዎች ሁኔታ በአንድ ጀምበር የማይፈታ እና መፍትሄዎቻቸው ከወታደራዊ ዘመቻዎች ሊገኙ አይችሉም ።” ብሏል፡፡
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ ሠራዊቱ "ሊባኖስ ውስጥ ከጦርነት ቀጠና ውጭ፣ በሚቆጣጠራቸው አምስት ቦታዎች እንደሚቆይ እና ማንኛውም የሂዝቦላ ጥሰት ቢኖር በኃይል እና ያለማወላወል ርምጃ ለመውሰድ መሥራቱን ይቀጥላል" ብለዋል ።
በኅዳር ወር መጨረሻ የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት፣ በሊባኖስ ከአንድ ዓመት በላይ የቆየውን ጦርነት አስቁሟል። ይህም የተኩስ አቁም ስምምነት ከመደረጉ በፊት በነበሩት ወራት ውስጥ የእስራኤል ወታደሮች ሊባኖስ ውስጥ የምድር ዘመቻ ሲያደርጉ እና በሂዝቦላ ላይ ተደጋጋሚ የአየር ድብደባ አጠናክረው ሲፈጽሙ ቆይተዋል።
የጋዛ ሰርጥ የሃማስ ታጣቂዎች ሰሜን እስራኤል ላይ ጥቃት በመፈጸም 1 ሺሕ 200 የሚጠጉ ሰዎችን ከገደሉ እና 250 ታጋቾችን ከወሰዱ አንድ ቀን በኋላ ታጣቂዎቹ እኤአ ጥቅምት 2023 በርካታ ድንበር ተሻጋሪ ሮኬቶችን መተኮስ ጀምረዋል፡፡
እስራኤል በሃማስ ላይ ባካሄደችው አጸፋዊ ጥቃት ከ48 ሺሕ 200 በላይ ፍልስጤማውያንን ተገድለዋል ሲል የጋዛ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገልጿል። ሚኒስቴሩ በታጣቂዎችና በሲቪሎች መካከል ያለውን የሟቾችን ቁጥር ለይቶ አላመለከተም፡፡ እስራኤል በበኩሏ ከ17 ሺሕ 000 በላይ ታጣቂዎችን መግደሏን አስታውቃለች።
የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት የመጀመሪያው ምዕራፍ በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ ያበቃል። እስካሁን ባለው የተኩስ አቁም ስምምነት፣ ሃማስ 24 ታጋቾችን መልቀቁን እና እስራኤል ከ1 ሺሕ በላይ የፍልስጤም እስረኞችን መፍታቷን ያካትታል።
መድረክ / ፎረም