በደቡባዊ ኦስትሪያ የምትገኘው ቪላች ከተማ አንድ ሰው ቀን ላይ ስድስት መንገደኞችን በስለት ወግቶ የ14 አመት ወንድ ልጅ ሲገድል አምስት ሰዎችን ደግሞ አቁስሏል፡፡
ጥቃቱን ያደርሰው የ23 ዓመቱ ተጠርጣሪ ብዙም ሳይቆይ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን፣ በኦስትሪያ የመኖሪያ ፍቃድ ያለው ሶሪያዊ እንደሆነ ተገልጿል።
በምግብ አቅራቢ ድርጅት ውስጥ የሚሠራ ሌላ ሶሪያዊ መኪናውን ወደ ተጠርጣሪው በመንዳት ጉዳቱን ለማስቆምና እንዳይባባስ ረድቷል ሲልም ፖሊስ አስታውቋል። የኦስትሪያ ነፃ የሶሪያ ማህበረሰብ ከጥቃቱ ራሱን ያገለለ መግለጫ አውጥቷል።
60ሽህ የሚጠጉ ነዋሪዎች በሚኖሩባት ከተማ ነዋሪዎቹ ጥቃቱ በተፈፀመበት ቦታ ላይ ሻማ አብርተዋል። የኦስትሪያው ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ቫን ደር ቤለን ጥቃቱን “አሰቃቂ” ሲሉ ገልጸውታል፡፡ የኦስትሪያ ነፃ የሶሪያ ማህበረሰብ በፌስቡክ በጥቃቱ እንደሌለበት በማሳወቅ ለተጎጂ ቤተሰቦች የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጿል።
የኦስትሪያ ባለስልጣናት የስለት ጥቃቱን "እስላማዊ የሽብር ክስተት" በማለት ፈርጀውታል። የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ጌርሃርድ ካርነር ዛሬ እንደተናገሩት "በዚህ ከተማ ውስጥ ንፁሃን ዜጎችን ያለ ልዩነት በጩቤ በገደለው እስላማዊ ጥቃት አድራሽ ቁጣ ተሰምቶኛል" ብለዋል።
ካርነር በቪላች ውስጥ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ጥቃት አድራሹ ከእስላማዊ መንግስት ቡድን ጋር ግንኙነት እንደነበረውና እራሱን በአጭር ጊዜ ውስጥ አክራሪ አድርጎ በቀጥታ ድህረገጾች ሲያቀርብ ነበር ብለዋል፡፡
ይህ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኦስትሪያ ውስጥ ሁለተኛው ገዳይ ጥቃት ነው። እ.ኤ.አ. በህዳር 2020፣ ከዚህ ቀደም እስላማዊ መንግስት ቡድንን ለመቀላቀል የሞከረ አንድ ሰው በቪየና ውስጥ ጥቃት አድርሶ እንደነበረ አሶሼትድ ፕሬስ አስታውሷል፡፡
መድረክ / ፎረም