በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሩዋንዳ የሚደገፉት አማጽያን ሁለተኛ ከተማ ያዙ 


 ምስራቃዊ ኮንጎ ቡካቩ የሚገኘው የነጻነት አደባባይ፡ የካቲት 8 2017 ዓ.ም፡፡ (AP Photo/Janvier Barhahiga)
ምስራቃዊ ኮንጎ ቡካቩ የሚገኘው የነጻነት አደባባይ፡ የካቲት 8 2017 ዓ.ም፡፡ (AP Photo/Janvier Barhahiga)

በሩዋንዳ የሚደገፉ አማፂያን ዛሬ ጥዋት በምስራቅ ኮንጎ ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ የሆነችውን ቡካቩን ይዘዋል፡፡

በአካባቢው ካለው የመንግስት ጦር ጥቂት መከላከል ብቻ የገጠማቸው አማጽያኑ በከተማዋ የሚገኘውን የደቡብ ኪቩ ግዛት አስተዳደር ፅህፈት ቤትን የተቆጣጠሩት ሲሆን አብዛኞቹም የአማፂያኑን ግስጋሴ በመፍራት ሸሽተዋል።

የኤም 23 አማፂያን በ101 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘውና ባለፈው ወር ከተቆጣጠሯት የጎማ ከተማ ለቀናት ተጉዘው ዛሬ እሁድ ጥዋት ማዕከላዊ ቡካቩ ደርሰው በከተማው ሲዘዋወሩና በርካታ ነዋሪዎች በደስታ ሲጮሁ የአሶሼትድ ፕሬስ ጋዜጠኞች ተመልክተዋል። ይሁን እንጂ በአብዛኛው የከተማው ክፍሎች የሚገኙ ቤቶች ነዋሪዎች የሌሉባቸው ባዶ ሁነዋል፡፡

የኤም 23 አማፅያን በማዕድን የበለፀገውን ምስራቃዊ የኮንጎ ክፍል ለመቆጣጠር ከሚሞክሩ ከአንድ መቶ በላይ ታጣቂ ቡድኖች ጎልተው ለመውጣት የቻሉ ሲሆን ከጎረቤት ሩዋንዳ በመጡ 4ሽህ ወታደሮች እንደሚደገፉም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡

አማፅያኑ 1.3 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ያለባትን ከተማ ሙሉ በሙሉ ስለመቆጣጠራቸው እስካሁን ግልጽ አልሆነም፡፡ ነገር ግን አመታትን ባስቆጠረው ውጊያ በማእከላዊ ቡካቩ መገኘታቸው ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ መስፋፋት ነው።

በጎርጎሪዮሳዊዉ 2012 ከብሄር ግጭት ጋር በተገናኘ በተደረገዉ ጦርነት ጎማን ብቻ ከተቆጣጠሩበት ጊዜ በተለየ በአሁኑ ወቅት አማፂያኑ የፖለቲካ ስልጣንን ለማግኘት ፍላጎት አላቸው ሲሉ ተንታኞች ይናገራሉ።

የአማጽያኑ ወደ ቡካቩ መገስገስ ተከትሎ ብዙ የኮንጐ ወታደሮች ቅዳሜ እለት ከሺህ ከሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች ጋር ሲሸሹ ታይተዋል።

የኮንጎው ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኬዲ በብዙ ርቀት በምትገኘው ዋና ከተማ ኪንሻሳ የፀጥታ ስብሰባ አካሂደዋል፡

የቡካቩ ከተማ በኤም 23 "የአጭር ጊዜ" ወረራ የተደረገባት ቢሆንም በኮንጎ ጦር ሰራዊት እና በአካባቢው ሚሊሻ አጋሮች ቁጥጥር ስር እንደሚገኝ ፕሬዝዳንቱ በኤክስ ገጻቸው አስታውቀዋል፡ ዛሬ በአብዛኛዎቹ የቡካቩ አካባቢዎች ምንም አይነት ውጊያ እንድሌለና የኮንጐ ሃይሎችም እንዳልታዩ የአሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ ያስረዳል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG