በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የ‍ዩናይትድ ስቴትስ እና የአውሮፓ ሀገራት አምባሳደሮች እና ተወካዮች በመቐለ


የዩናይትድ ስቴትስ፣ የብሪታንያ፣ የጀርመን፣ የጣልያን፣ የፈረንሳይ እና የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደሮች እና ተወካዮች
የዩናይትድ ስቴትስ፣ የብሪታንያ፣ የጀርመን፣ የጣልያን፣ የፈረንሳይ እና የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደሮች እና ተወካዮች

የዩናይትድ ስቴትስ፣ የብሪታንያ፣ የጀርመን፣ የጣልያን፣ የፈረንሳይ እና የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደሮች እና ተወካዮች ከትግራይ ክልል ጊዝያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ እና ከህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ጋራ ተወያዩ።

በኢትዮጵያ የዩናትድ ስቴትስ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ፣ ማክሰኞ የካቲት 4 ቀን 2017 ዓ.ም የዩናይትድ ስቴትስ፣ የታላቋ ብሪታንያ፣ ጀርመን፣ ጣልያን፣ ፈረንሳይ እና አውሮፓ ኅብረት አምባሳደሮች እና ተወካዮች በፕሪቶሪያ የተፈረመው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት አስመልከቶ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ እና ከህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ጋራ ተገናኝተው እንደተወያዩ አስታውቋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ በወ‍ይይቱ ወቅት "የፕሪቶርያው ስምምነት በምልዓት ባለመተግበሩ ተፈናቃዮችን ለመመለስ አልተቻለም፣ የትግራይን ችግርም ለመፍታትም አልተቻለም" ሲሉ ለልዑካኑ ተናግረዋል።

“በፕሪቶሪያ የተፈረመው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት ትግበራ ላይ ያሉት ለውጦች እና በትግበራው የሚያጋጥሙ እንቅፋቶችን አስመልክቶ ከአሁን በፊት ያካሄደነው ውይይት ተከታይ ነው። በዚህ ውይይትም የሚያጋጥሙን ችግሮች መፍትሄ ለማስገኘት ያግዛል። የስምምነቱ አንኳር የሆነው ተፈናቃዮች ወደ ቀየ መመለስ አለመፈፀም አሁን የገጠመን ችግር ነው። በትግራይ በአሁኑ ግዜ ያለው ፖለቲካዊ ቀውስ መነሻውም ይህ አለመፈፀሙ ነው።” ብለዋል አቶ ጌታቸው።

ልዑካኑን የመሩት በኢትዮጵያ የብሪታኒያ አምባሳደር ዳረን ዊልች በበኩላቸው፣ "የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች በብዛት ሆነው ወደ መቐለ የተጓዙት የፕሪቶሪያው ሰምምነት በምልዓት እንዲተገበር ባላቸው ፍላጎት ነው" በማለት አስረድተዋል።

"መምጣታችን ግጭትን በዘላቂነት ለማቆም የተደረሰው ስምምነት በተሻለ መልኩ እንዲተገበር ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ እንደሚፈልግ ማሳያ ነው። ስምምነቱ እንደግፋለን። የስምምነቱ ትግበራ ብዙዎች እንደሚሹት በፍጥነት እየተተገበረ እንዳልሆነ እንረዳለን። ይህ ውይይታችን ስለሁኔታው በተሻለ ለመረዳት ያግዘናል፣ እንዲሁም ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ስምምነቱን ለመፈፀም የሚጠበቅበትን እገዛም እንድንመለከት ያግዛል” ብለዋል አምባሳደሩ።

ልዑካኑ ከህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረሚካኤል ጋራም እንደተወያዩ ፓርቲው በፌስቡክ ገፁ አስታውቋል።

ዶክተር ደብረፅዮን በውይይቱ የፕሪቶርያ ስምምነት በምልዓት ባለመተግበሩ የክልሉ ህዝብ ስቃይ፣ መከራ እና እንግልት ቀጥሏል። ተፈናቃዮች በመጠለያ ካምፕ እየተንገላቱ ይገኛሉ" በማለት ለልዑካኑ ገልፀውላቸዋል።

የስምምነቱ መተግበር ለዘላቂ ሰላም ትልቅ ሚና እንዳለውም አስረድተዋል።

የትግራይ የወሰን አስተዳደር ወደ ቅደመ ጦርነት እንዲመለስ፣ ተፈናቃዮች እንዲመለሱ እና የክልሉ የመልሶ ግንባታ ሥራ እንዲጀመር ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና እንዲያሳድር ጠይቀዋል።

ልዑካኑ በመቐለ ሰብዓ ካሬ ተብሎ የሚያወቀውን የተፈናቃኖች ካምፕ ጎብኝተዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG