የትራምፕ አስተዳደር “ የጃኑዋሪ 6 ጉዳይ” በመባል በሚታወቀው ከአራት አመት በፊት የተካሄደውን ምርጫ ውጤትን ተከትሎ በዩናይትድስ ስቴትስ ምክር ቤት ሕንፃ ላይ በደረሰው ጥቃት ዙርያ ምርመራ ላይ የተሳተፉ አቃቢያነ ህጎችን ከስራ አባሯል፡፡
በዚህ ሂደት ተሳትፎ የነበራቸው የፌደራል ምርመራ ቢሮ ኤፍ ቢ አይ መርማሪዎች ስም ዝርዝር እንዲሰጠውም የጠየቀ ሲሆን እነርሱም ተመሳሳይ እጣፈንታ ይገጥማቸዋል ተብሏል፡፡
ርምጃውም ኋይት ሃውስ በፌዴራል ህግ አስከባሪ አካላት ላይ ቁጥጥር ለማድረግና በቂ ታማኝነት የጎደላቸው ተደርገው የሚታዩ ሰራተኞችን ከኤጀንሲዎች የማጥራት ውሳኔዎችን የሚያንፀባርቅ እንቅስቃሴ ተደርጎ ተወስዷል፡፡
ተጠባባቂ ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ኤሚል ቦቭ በዩናይትድ ስቴትስ ካፒቶል ጥቃት ለተከሰሱት ከ1ሽህ 500 በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርገውን የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የምህረት እርምጃ ተከትሎ የጥር 6 ጉዳይን ይዘው የነበሩ አቃቤ ህጎች ከስራ እንዲባረሩ ትእዛዝ ማስተላለፋቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ያገኘውን ማስታወሻ መሰርት አድርጎ ዘግቧል፡፡
በዋሽንግተን በሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ አቃቤ ህግ ቢሮ ውስጥ ሁለት ደርዘን የሚጠጉ ሰራተኞች ስራቸው እንዲቋረጥ መደረጉን ጉዳዩን የሚያውቁና በዚህ ጉዳይ ላይ ለመናገር ፈቃድ ስለሌላቸው ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ ሰው ተናግረዋል፡፡
በተጠባባቂ ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ቦቭ በተላከ ሌላ ማስታወሻ ከግማሽ ደርዘን በላይ የሚሆኑ የኤፍቢአይ ከፍተኛ አመራሮችን እስከ ሰኞ ድረስ ጡረታ እንዲወጡ ወይም እንዲባረሩ የታዘዙ ሲሆን በጥር 6 ላይ በምርመራ ላይ የተሳተፉትን የኤፍ ቢ አይ ሰራተኞችን ስም ፣ ማዕረግ እና ቢሮ ጠይቋል ።
አስተዳደሩን ከመቀላቀላቸው በፊት ትራምፕን በወንጀል ጉዳያቸው የተከላከሉት ቦቭ የፍትህ ዲፓርትመንት ባለስልጣናት “ተጨማሪ እርምጃዎች አስፈላጊ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የሰራተኞች የግምገማ ሂደትን ያካሂዳሉ” ሲሉም አስታውቀዋል፡፡
መድረክ / ፎረም