በእስራኤል እና በፍልስጤም ታጣቂ ቡድን መካከል ያለውን ግጭት ለማስቆም በተደረሰሰው ስምምነት መሰረት ሃማስ ሶስት የእስራኤል ታጋቾችን ዛሬ ለቋል፡፡
የ54 አመቱ ፈረንሣይ-እስራኤላዊው ኦፌር ካልዴሮንና የ35 ዓመቱ ያርደን ቢባስ፣ ወደ እስራኤል ከመመለሳቸው በፊት በደቡብ የጋዛ ከተማ ካን ዮኒስ ለቀይ መስቀል ተሰጥተዋል። የ65 አመቱ እስራኤላዊ-አሜሪካዊ ኪት ሲጄል ደግሞ ከሰዓታት በኋላ በጋዛ ከተማ ከሚገኝ ወደብ ተለቋል።
በአራተኛው የታጋቾችና እስረኞች ልውውጥ እስራኤል 90 እስረኞችን ለመልቀቅ ተስማምታ የነበረች ሲሆን አንድ የፍልስጤም ተሟጋች ቡድን በበኩሉ የሚለቀቁት ፍልስጤማውያን ቁጥር ወደ 183 መሻሻሉን አስታውቋል፡፡
ሃሙስ እለት ሃማስ ሶስት እስራኤላውያንን እና አምስት የታይላንድ ዜጎችን ጨምሮ 8 ታጋቾችን የለቀቀ ሲሆን በእለቱ እስራኤል ደግሞ 110 የፍልስጤም እስረኞችን ፈታለች፡፡ ከተፈቱት መካከል 32ቱ የእድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸው ነበሩ፡፡
የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተከትሎ እስካሁን ከ423ሽህ በላይ ፍልስጤማውያን ወደ ሰሜናዊ ጋዛ ተመልሰዋል። እ.ኤ.አ. በጥቅምት 2023 በእስራኤል-ሀማስ ጦርነት መጀመሪያ ላይ የእስራኤል ጦር ከግዛቱ እንዲወጡ በማዛዙ ተሰደው የነበሩት ናቸው፡፡
ትላንት በጄኔቫ የአለም የምግብ ፕሮግራም ወደ ጋዛ ሰብአዊ ርዳታ ለማድረስ በሚደረገው ጥረት ላይ በሰጠው መግለጫ የተቋሙ የአካባቢው ሃላፊ የሆኑት አንትዋን ሬናርድ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ኤጀንሲው የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰበት ጊዜ ጀምሮ ከ32ሽህ ሜትሪክ ቶን በላይ ምግብ ለጋዛ ማቅረቡን ተናግረዋል፡፡
ይህ መጠንም በታህሳስ ወር ከቀረበው በእጥፍ እና በጥቅምት ወር ከቀረበው በሶስት እጥፍ ይበልጣል ብለዋል። ሬናርድ የአለም ምግብ ፕሮግራም እስካሁን 300ሽህ ሰዎች ተደራሽ ማድረጉንም አስታውቀዋል፡፡
መድረክ / ፎረም