ፕሬዘዳንት ትራምፕ በዓለ ሲመት ከመፈጸማቸው ባሉት 30 ቀናት ውስጥ ከፌዴራል ሠራተኞች ጋር የተደረገ ማንኛውም የጋራ ስምምነት ተቀባይነት አይኖረውም አሉ። ይህም ፕሬዝደንቱ የፌደራል ተቋማትን የሰው ሃይል መልሶ ለማቋቋም እያደረጉት ያለው የቅርብ ጊዜ ጥረት አካል ነው፡፡
ትራምፕ ለሁሉም የሥራ አስፈፃሚ ክፍሎች እና ኤጀንሲዎች ኃላፊዎች በላኩት ማስታወሻ ላይ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በመጨረሻዎቹ ቀናት ከፌዴራል ሰራተኞች ጋር የተደረጉ የጋራ ስምምነቶችን ሆን ብሎ ማጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡
“ አባካኝ እና ያልተሳኩ ፖሊሲዎችን ከስልጣን ማብቃት በኋላም በማራዘም አስተዳዳሬን ለመጉዳት የተደረገ ጥረት ነው " ብለዋል፡፡
በአዲሱ ፖሊሲ ምን ያህል ስምምነቶች እንደሚነኩ እስካሁን አልታወቀም፡፡ የጋራ ድርድር ስምምነቶች በሠራተኛ ማህበራትና በሠራተኞቻቸው መካከል የሥራ ሁኔታዎችን ፣ ክፍያን እና ሌሎች ፖሊሲዎችን የሚገልጹ ስምምነቶች ናቸው።
ርምጃው የመጣው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቢሮክራሲውን ለመቀነስና በብዙ ታማኞች ለማዋቀር ባደረጉት የመጀመሪያ እርምጃቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ የመንግስት ሰራተኞችን ከስራ በማባረር እና ገሸሽ በማድረግ የአሜሪካ መንግስት መዋቅር ላይ ትልቅ ለውጥ በጀመሩበት ወቅት ነው።
መድረክ / ፎረም