አምባሳድር ብናልፍ አንዱአለም በዩናይትድ ስቴትስ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው መሾማቸውን የሀገር ውስጥ ብዙኅን መገናኛ ዘግበዋል።
ዛሬ ከኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ የሹመት ደብዳቤ እና የሥራ መመሪያ የተቀበሉት አምባሳደር ብናልፍ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ቴዎድሮስ ምሕረት አማካኝነት ቃለ መሐላ መፈፀማቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አመልክቷል።
አምባሳደር ብናልፍ ቀደም ሲል የኢትዮጵያ የሰላም ሚኒስቴር ሆነው ያገለገሉ ሲኾን ከብሔራዊ ደኅንነት እና ሰላም ግንባታ ጋራ በተያያዙ የመንግስት እንቅስቃሴዎች ውስጥም ተሳትፈዋል።
ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲን በአምባሳደርነት ሲያገለግሎ የቆዩት አምባሳደር ስለሺ በቀለ ከለቀቁ በኋላ ኢምባሲው በጉዳይ ፈጻሚነ ሲመራ ቆይቷል።
አምባሳደር ብናልፍ ሥራቸውን በይፋ ከመጀመራቸው በፊት የሹመት ደብዳቤያቸውን ለዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል። ኢትዮጵያን በመወከል ከዩናትይድ ስቴትስ ጋራ በሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶች ውስጥ እንዲሳተፉና፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩበት ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ የዕለት ተዕለት ሥራም እንዲመሩ ኃላፊነት እንደተሰጣቸው ፕሬዝዳንቱን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ታዬ ሹመቱን በሰጡበት ወቅት፣ በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ያለውን የረጅም ዘመን ግንኙነት የሚመጥን ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ መግለጻቸውን ያመለከተው የዜና ተቋሙ አምባሳደር ብናልፍ ይህን ታሳቢ ያደረገ አመራር እንዲሰጡ ማሳሰባቸውን አመልክቷል።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ እና አስተዳደራዊ ዘርፎች በርካታ የአመራር ቦታዎች ላይ ያገለገሉት አምባሳደር ብናልፍ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ በመሆን በሚኒስትርነት ማዕረግ ያገለገልሉ ሲሆን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሥር የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሆነውም ሠርተዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዲግ) ወደ ብልፅግና ፓርቲ ከመቀየሩ በፊትም፣ በአማራ ክልል መንግሥት ውስጥ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በመኾን እና የክልሉን ትምህርት ቢሮ በመምራት አገልግለዋል።
መድረክ / ፎረም