የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ሰነድ አልባ ስደተኞችን ኪዩባ በሚገኘው ጓንታናሞ ቤይ እንዲያዙ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል። ለዚህም አስተዳደራቸው እስር ቤቱን ዝግጁ እንዲያደርግ የሚያስችል ሰነድ እንደፈረሙም ታውቋል።
በኪዩባ የሚገኘው የአሜሪካ እስር ቤት፣ ጓንታናሞ ቤይ፤ ወታደራዊ እስረኞችን፣ የታሊባንና የመስከረም 11 የሽብር ጥቃት ተጠርጣሪዎችን በመያዙ ይታወቃል።
የመከላከያ እና የሃገር ውስጥ ደህንነት መሥሪያ ቤቶች እስር ቤቱ 30 ሺሕ ስደተኞችን ለማስተናገድ እንዲችል ዝግጅት እንዲያደርጉም ትረምፕ አዘዋል።
አንዳንዶቹ ስደተኞች ከፍተኛ ወንጀል የፈጸሙ በመሆኑና፣ የሃገራቸው መንግሥት አግቶ ያቆያቸዋል የሚል እምነት ስለሌላቸው፣ ወደ ጓንታናሞ እንድሚልኳቸው ትረምፕ አስታውቀዋል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የዋይት ሃውስ ባለሥልጣን፣ ትረምፕ ጓንታናሞን የተመለከተውን ሰነድ ቀድመው መፈረማቸውን ተናግረዋል።
ሰነዱ ከተለመደው ፕሬዝደንታዊ ትዕዛዝ ለየት ያለ እና ‘ፌዴራል ሬጂስተር’ ተብሎ ለሚታወቀውና የመንግስት ሰነዶችን ለሚያትመው መሥሪያ ቤት እንደማይላክም ታውቋል።
ለዕቅዱ ማስፈጸሚያ ገንዘብ እንዲመደብ ለማድረግ የአሜሪካ ምክር ቤት ይሁንታ እንደሚያስፈልገውም ታውቋል።
መድረክ / ፎረም