በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሲ ዲ ሲ ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር በመተባበር የሚያካሂዳቸውን ሥራዎች በአስቸኳይ እንዲያቆም ታዘዘ


ፋይል - በጆርጂያ ግዛት፣ አትላንታ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታዎች መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ተቋም
ፋይል - በጆርጂያ ግዛት፣ አትላንታ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታዎች መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ተቋም

የዩናይትድ ስቴትስ የጤና ባለሥልጣናት ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር የሚሠሯቸውን ሥራዎች በአስቸኳይ እንዲያቆሙ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል።

ድንገተኛው ትዕዛዝ ያተኮረው በዩናይትድ ስቴትስ የበሽታዎች መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ተቋም ላይ ሲሆን የተቋሙ ባለሥልጣን የሆኑት ጆን ኒኬንጋሶንግ ለከፍተኛ አመራሮች ዕሁድ ማታ በላኩት ማሳሰቢያ ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር የሚሠሩ የተቋሙ ሠራተኞች በአስቸኳይ አቁመው ቀጣይ መመሪያ እስከሚሰጥ እንዲጠብቁ ማዘዛቸውን መመሪያውን የተመለከተው አሶሲየትድ ፕሬስ ዘግቧል።

የጤና ጥበቃ አዋቂ ባለሞያዎች ድንገተኛው ትዕዛዝ አፍሪካ ውስጥ ማርበርግ ቫይረስ እና ኤምፖክስ የመሳሰሉ ወረርሽኞችን እና ሌሎችንም ዓለም አቀፍ የጤና ስጋቶችለመቆጣጠር የሚደረጉ ጥረቶች እና ምርምሮችን ያስተጓጉላል የሚል ስጋት እንዳላቸው አመልክተዋል።

ትዕዛዙ የተሰጠው በዓለም ዙሪያ ያሉ የጤና ባለሥልጣናት በአሜሪካ እንስሳት ላይ የተቀሰቀሰውን የአእዋፍ ወረርሽኝ ለመከታተል ጥረት እያደረጉ ባለበት በዚህ ወቅት መሆኑ ተጠቁሟል።

የተላለፈው መመሪያ ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር በትብብር የሚሠሩ ሥራዎች በሙሉ እንዲቋረጡ የሚያዝ ሲሆን የድርጅቱ መሥሪያ ቤቶች በአካል መጎብኘትም ይሁን በኢንተርኔት አማካይነት መገናኘት ይከለክላል።

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ዩናይትድ ስቴትስን ከዓለም የጤና ድርጅት አባልነት የማስወጣት ሂደት እንዲጀመር ባለፈው ሳምንት አስፈጻሚ ትዕዛዝ የፈረሙ ቢሆንም ሂደቱ ወዲያውኑ አልተጀመረም።

ከዓለሙ የጤና ድርጅት እንድትወጣ የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት መፍቀድ አለበት። እስከዛ አሜሪካ የዓመቱን ክፍያዋን መፈጸም ያለባት ሲሆን ከድርጅቱ ለመውጣት የአንድ ዓመት ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ መስጠት ይኖርባታል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG