በእስራኤል እና በሐማስ ጦርነት የተፈናቀሉ ከሦስት መቶ ሺህ የሚበልጡ ፍልስጥኤማዊያን ተፈናቃዮች ትላንት ሰኞ ወደ ሰሜናዊ ጋዛ መመለሳቸውን በሐማስ የሚመራው የጋዛ ሰርጥ መንግሥት ባለስልጣናት ተናገሩ።
ተፈናቃዮቹ የተመለሱት እስራኤል የፍተሻ ኬላዎቹን ከፍታ እንዲመለሱ መፍቀዷን ተከትሎ ነው። ፍልስጥኤማዊያኑ አብዛኞቹ በእግራቸው የቻሉትን ያህል ዕቃ ተሸክመው ጦርነቱ እንደተጀመረ ጥለውት ወደሸሹት እና ይኑር ይፍረስ ወደማያውቁት የቀድሞ መኖሪያቸው ተጉዘዋል። እስራኤል የሐማስ ታጣቂዎችን እና ፈንጂ ያጠመዱባቸውን ህንጻዎች ዒላማ አድርጋ ባደረሰችው የቦምብ ድብደባ አብዛኛው አካባቢ ወድሟል።
እስራኤል እ አ አ በ2023 ጥቅምት ውስጥ ጥቃቱን እንደጀመረች ወደአንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ነዋሪዎች ከሰሜናዊ ጋዛ እንዲወጡ ማዘዟ ሲታወስ ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው እንዲመለሱ ለመጀመሪያ ጊዜ መፈቀዱ ነው።
ፍልስጥኤማዊያኑ ወደጋዛ ከተማ የተመለሱት በእስራኤል እና በሐማስ የተደረሰው የስድስት ሳምንታት የተኩስ አቁም የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ ባለበት በአሁኑ ወቅት መሆኑ ነው። የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተከትሎ እስካሁን ሰባት ታጋቾች ከጋዛ ሲለቀቁ እስራኤል ሦስት መቶ የሚሆኑ ፍልስጥኤማዊያን እሥረኞች ለቅቃለች። ሰብዓዊ ረድዔትም በብዛት ወደጋዛ መግባት ጀምሯል።
ትላንት እስራኤል እንዳለችው ሐማስ በመጀመሪያው የተኩሥ አቁም ውሉ ምዕራፍ ስለሚለቀቁት ታጋቾች እና ከቀሩት ታጋቾቹ መካከል ስምንቱ በሕይወት እንደሌሉ አሳውቋታል። ሐማስ ተጨማሪ ታጋቾችን በቀጣዮቹ ቀናት ውስጥ እንደሚለቅቅ ተመልክቷል።
ይህ በዚህ እንዳለ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ " ጋዛን ለማጽዳት የሚደረገው " ሲሉ በገለጹት ጥረት ዮርዳኖስ እና ግብጽ ተጨማሪ ፍልስጥኤማዊያን ተፈናቃዮችን እንዲቀበሉ የሚፈልጉ መሆኑን ተናግረዋል። ሆኖም ሁለቱ ሀገሮች ብቸኛው የመፍትሄ እርምጃ ከእስራኤል ጎን ለጎን የፍልስጤም መንግሥት መመሥረት ብቻ መሆኑን በማመልከት ሃሳቡን ውድቅ አድርገውታል።
ዩናይትድ ስቴትስ የፍልስጤም አገረ መንግሥት መቋቋምን ሃሳብ ለረጅም ጊዜ ስትደግፍ ቆይታለች። የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ግን ይቃወማሉ።
መድረክ / ፎረም