በሩዋንዳ የሚታገዘው ኤም 23 የተባለው ታጣቂ ቡድን ቁልፍ የሆነችውን የምሥራቅ ኮንጎ ዋና ከተማ ተቆጣጥሬአለሁ ማለቱን ተከትሎ ዩናይትድ ስቴትስ ድርጊቱን አውግዛለች።
በተያያዘ ዜና የኬኒያ ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ ከዲሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት ፌሊክስ ቲሺኬሴዲ እና ከሩዋንዳው ፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ ቀውሱን በሚመለከት ነገ ረቡዕ ለመወያየት ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር እንዳስታወቀው ትላንት ሰኞ የዲሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት ቲሺሴኬዲን በስልክ ያነጋገሯቸው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማርኮ ሩቢዮ " በሩዋንዳ የሚታገዘው ኤም 23 ጎማ ላይ ያደረሰውን ጥቃት አውግዘዋል። ዩናይትድ ስቴትስ የዲሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክን ሉዓላዊነት እንደምታከብር አረጋግጠውላቸዋል" ብሏል።
ግጭቱ ወታደራዊ መፍትሄ የማይገኝለት እንደሆነ የጠቆሙት የኬኒያ ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ፕሬዝደንት ሺሴኬዲ እና ፕሬዝደንት ካጋሜ ነገ ረቡዕ ለመወያየት እንደተስማሙ አመልክተዋል።
ይህ በዚህ እንዳለ ታጣቂው ቡድን ጎማን እንደያዘ ከተናገረም በኋላ ከተማዋ ውስጥ በቡድኑ እና በኮንጎ ኃይሎች መካከል ውጊያው እንደቀጠለ መሆኑን ኮንጎ የሚገኙ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ ባለሥልጣን ትላንት ሰኞ ተናግረዋል።
ኮንጎ ተቀማጩ የመንግሥታቱ ድርጅት አስተባባሪ ብሩኖ ለማርኪስ ከኪንሳሻ በሰጡት ቃል ውጊያው ጎማ ውስጥ በሁሉም አቅጣጫ መስፋፋቱን ጠቁመው ሁኔታው እጅግ አደገኛ እንደሆነ ገልጸዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት፥ የድርጅቱ ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ እና ሌሎችም የድርጅቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ታጣቂው ቡድን በአስቸኳይ ውጊያ እንዲያቆም እና ከያዛቸው ግዛቶች እንዲወጣ ጠይቀዋል። የሩዋንዳ ኃይሎችም እንዲወጡ የጠየቁት ባለሥልጣናቱ ሁለቱ ወገኖች የአንጎላ ፕሬዝደንት ዡዋው ሎሬንሶ ወደሚመሩት የሽምግልና ሂደት እንዲመለሱ አሳስበዋል።
መድረክ / ፎረም