በሱዳን ሰሜን ዳርፉር ክልል ውስጥ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ላይ፤ በሰው አልባ አውሮፕላኖች አማካኝነት በተፈጸመ ጥቃት ከ70 በላይ ሰዎች ሲሞቱ በደርዘን የሚቆጠሩ መቁሰላቸውን ተከትሎ፤ የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ትላንት ቅዳሜ በሱዳን በጤና ጥበቃ ሰራተኞች እና ተቋማት ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት እንዲያቆም አሳሰበዋል።
አርብ ዕለት የተቋሙ አባላት የስራ ማቆም አድማ ካደረጉ በኋላ፤ የአለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ገብረእየሱስ “የሳውዲ ማስተማሪያ እና የእናቶች ሆስፒታል የማህጸን እና የጽንስ ህክምናን ጨምሮ፣ የውስጥ ደዌ ህክምና፣ የቀዶ ጥገና፣ የህፃናት ህክምና እና እንዲሁም ከተመጣጠነ ምግብን ማከፋፈል አገልግሎት የሚሰጥ ብቸኛው በኤል ፋሸር የሚገኝ ሆስፒታል እንደመሆኑ መረጋጋት ሊኖረው ይገባል” በማለት በኤክስ ማኅበራዊ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ዶ/ር ቴድሮስ አያይዘውም "በሱዳን የተጎዱት ተቋማት በፍጥነት ወደ ነበሩበት ተመልሰው ሙሉ አገልግሎት እንዲሰጡ፤ በጤና ጥበቃ ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ሁሉ እንዲቆሙ ጥሪያችንን እንቀጥላለን" ብለዋል።
የሱዳን ግጭት በአመዛኙ በፈጥኖ ደራሽ ቡድኑ ተነሳሽነት በብሄር የሚመራ ብጥብጦችን በመፍጠር ትልቅ ሰብዓዊ ቀውስ አስከትሏል።
የዳርፉር ሀገረ ገዥ ሚኒ ሚናዊ በኤክስ ማኅበራዊ ገጻቸው ላይ እንደተናገሩት በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ቡድን የተተኮሱ ሰው አልባ አውሮፕላኖች በሰሜን ዳርፉር ዋና ከተማ የሚገኘውን የሆስፒታሉን ድንገተኛ ክፍል በማጥቃታቸው፣ ሴቶችን እና ህጻናትን ጨምሮ ታካሚዎች ሞተዋል በማለት አስታውቀዋል።
መድረክ / ፎረም