በሱዳን ዳርፉር ግዛት ኤል ፋሸር ውስጥ ስራ ላይ ከሚገኙት ጥቂት ሆስፒታሎች በአንዱ በሰው አልባ አውሮፕላን በደረሰ ጥቃት 30 ሰዎች መሞታቸውን እና በርካቶች መቁሰላቸውን የህክምና ምንጮች ዛሬ አስታውቀዋል፡፡
አርብ ማምሻውን በሳውዲ ሆስፒታል ላይ በደረሰው በበዚህ የቦምብ ጥቃት የድንገተኛ አደጋ ህክምና የሚሰጥበት የሆስፒታሉ ህንጻን "ለውድመት ዳርጓል" ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የመረጃው ምንጭ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል፡፡
ከሁለቱ የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች የትኛው ጥቃቱን እንዳደረሰ እስካሁን አልታወቀም።
ከእአአ ሚያዝያ 2023 ጀምሮ ሰፊውን የዳርፉርን ግዛት ከያዘው የፈጥኖ ደራሹ ሃይል ጋር የሱዳን ጦር ሲዋጋ ቆይቷል፡፡
እንደ የሕክምና የመረጃ ምንጭ ከሆነ፣ ይኸው ሕንፃ “ከጥቂት ሳምንታት በፊት” በፈጥኖ ደራሽ ሰው አልባ አውሮፕላን ተመትቶ ነበር።
በኤል-ፋሸር የጤና ተቋማት ላይ ጥቃቶች መበራከታቸው ሲገለጽ ፣የህክምና በጎ አድራጎት ድርጅት የሆነው ድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን የሳዑዲ ሆስፒታል “አሁን የቀረ የቀዶ ህክምና የሚሰጥበት ብቸኛው የህዝብ ሆስፒታል ነው” ሲል በዚህ ወር አስታውቋል፡፡
በመላ አገሪቱ እስከ 80 በመቶ የሚደርሱ የጤና አጠባበቅ ተቋማት ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆኑ መደረጋቸውን ይፋዊ አኃዛዊ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ጦርነቱ እስካሁን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩትን ሱዳናውያንን ለሞት ሲዳርግ፣ ከ12 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑትን ደግሞ አፈናቅሏል፡፡
መድረክ / ፎረም