የዋይት ኃውስ ድረ ገጽ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመላከተው፤ በጎርጎርሳውያኑ 2022 ዩናይትድ ስቴትስ በአፍሪካ 11.5 ቢሊየን ዶላር ለኤች አይቪ ኤድስ ድጋፍ፤ እንዲሁም ሁለት ቢሊየን ዶላር ደግሞ ለቤተሰብ ምጣኔና፣ ለስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት አቅርቦቶች፣ የእናቶች እና ጨቅላ ህጻናት ጤና ላይ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቋል።
ይሁን እንጂ ይህ አቅርቦት የ47ኛው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዘዳንት ሆነው ወደ ሥልጣን በተመለሱት ዶናልድ ትራምፕ በሀገር ውስጥ ሮ እና ዌድ ተብሎ በሚጠራው የጽንስ ማቋረጥን ከሚከለክለው መብት ጋር ተያይዞ ያላቸው አቋም የተነሳ የጽንስ ማቋረጥ አገልግሎት በሚሰጡ አለም አቀፍ አጋሮቻቸውን ለስጋት ዳርጓል። ፕሬዝዳንቱ ወደ ሥልጣን በመጡ ዕለት ሀገራቸው ከአለም የጤና ተቋም ጋር ያላትን ግንኙነት ማቋረጣቸው ዩናይትድ ስቴትስ ከስነ ተዋልዶ ጤና ጋር የሚኖራት አቋም እንደሚያጠራጥር ባለሞያው ይገልጻሉ፡፡
በኢትዮጵያ የማሪ ስቶፕስ ኢንተርናሽናል ዳይሬክተር ዶ/ር አበበ ሽብሩ የስነ ተዋልዶ ጤና ድጋፍ መቋረጥ በጽንስ ማቋረጥ ብቻ ሳይሆን፤ ይህን አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በሚያደርጓቸው በኤች አይ ቪ ኤድስ መድሃኒት ተደራሽነት ላይ ጭምር ጫና ያሳድራል ይላሉ።
በሌላ በኩል ገርማቸር ተቋም ከፍተኛ የስነተዋልዶ ጤና ሳይንስ ተመራማሪ. የሆኑት ኤሊዛቤት ሱሊ በአለም ዙሪያ ያሉ የዩናይትድ ስቴትስን ድጋፍ የሚቀበሉ ሀገራት እና የጤና ሚንስትሮች፤ በትራምፕ አስተዳደር ሊከሰት ለሚችል የስነ ተዋልዶ ጤና ድጋፍ መስተጓጎል እንዲዘጋጁ ይመክራሉ።
በተጨማሪም ወሲባዊ እና የስነ ተዋልዶ መብቶችን በመቃወም የሚታወቁት የዩናይትድ ስቴትስ የክርስቲያን መብት ቡድኖች ከጎሮጎሳውያኑ 2019 ጀምሮ በአፍሪካ ያላቸውን ድጋፍ እና እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመራቸውን፤ የጋዜጠኝነት እና ማህበራዊ ለውጥ ኢንስቲትዩት (IJSC) አዲስ የመረጃ ትንተና አመልክቷል።
አለም አቀፉ ማሪ ስቶፕስ ኢንተርናሽናል የጽንስ ማቋረጥ አገልግሎትን እንደማያቋርጥ እና ይህን ተክትሎ ሊቋረጡ ለሚችሉ ድጋፎች እየተዘጋጀ መሆኑን የተቋሙ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶ/ር አበበ ሽብሩ ገልጸዋል።
መድረክ / ፎረም