ትረምፕ ለመጀመሪያ ጊዜ አከታትለው በአወጧቸው የመጀመሪያ ቀን የአስፈፃሚ ትዕዛዞች ፣ አብዛኞቹን የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ውሳኔዎችን ሰርዘዋል። በኢሚግሬሽን፣ ዩናይትድ ስቴትስን ከፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነትና ከዓለም ጤና ድርጅት ማውጣት፣ እንዲሁም ቲክ ቶክን አሜሪካ ውስጥ እንዲቆይ ማድረግ ከብዙዎቹ መካከል ይገኙበታል፡፡
እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ጥር 2021 ዓ.ም በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ህንጻ (ካፒቶል) ላይ በደረሰው ጥቃት ለተሳተፉ ሰዎችም ይቅርታ አድርገዋል።
ትረምፕ እ.ኤ.አ. በ 2024 የምርጫ ዘመቻ ወቅት ደጋግመው ቃል በገቡት መሰረት፣ እኤአ 2020 ባይደን ትረምፕን ካሸነፉበት የምርጫ ውጤት ጋራ በተያያዘ፣ እኤአ ጥር 6 ቀን በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ህንጻ ላይ፣ በተፈጸመ ጥቃት ተከሰው ለተፈረደባቸው 1 ሺሕ 500 ለሚሆኑ ወይም በወንጀል የተከሰሱ ሰዎችን በይቅርታ ምረዋል።
በባይደን አስተዳደር “የፖለቲካ ተቃዋሚዎች” ማለትም የትረምፕ ደጋፊዎች ላይ የፌዴራሉ መንግሥት የመሰረታቸውን ክሶች እንዲያቆምም አዘዋል፡፡
ትረምፕ ትላንት ሰኞ ምሽት በካፒታል አሬና ለቴሌቪዥን በተሰናዳ ዝግጅት ላይ እያንዳንዱ የፌዴራል መንግሥት ተቋም፣ ለሸማቾች የዋጋ ንረትን በመዋጋት እንዲሠራ ሲሉ በገለፁት መመሪያ ላይ ፈርመዋል።
መመሪያው እንደሌሌቹ በግልጽ የሚያስቀምጠው የአስፈጻሚነት ውሳኔ ባይኖረውም የሚሰጠውን ትኩረት እንዲያሳይ የተላለፈ መኾኑን አሶሽየትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ትረምፕ የባደን ርምጃዎችን በመሰረዝ እና የራሳቸውን ትዕዛዞች በማከል ፣ የሁሉንም የፍጆታ ዕቃዎች ወጪዎችን እንደሚቀንሱ ቃል በገቡት መሠረት፣ በነዳጅ ዘይት እና በተፈጥሮ ጋዝ ምርት ላይ የተጣሉ የቁጥጥር ጫናዎችን እያቃለሉ ነው፡፡ ትረምፕ በተለይ የቅሪተ አካል ነዳጅ ምርትን ለመጨመር ልዩ ትኩረታቸውን አላስካ ላይ አድርገዋል።
ትረምፕ አስቸኳይ የኃይል አቅርቦት አዋጅ ያወጡ ሲሆን ቃል በገቡት መሰረት ያለንን ነዳጅ ቆፍረን በማውጣት እንጠቀማለን ብለዋል፡፡ ባይደን የበካይ ጋዝን ለመቀነስ በአንዳንድ አካባቢዎች ከሚመረቱ ተሽከርካሪዎች በኤሌክትሪ የሚሠሩ በተወሰነ መጠን ድርሻውን እንዲይዙ ያወጡትን ፖሊሲ ሽረዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በንግዱም ዘርፍ እኤአ ከየካቲት 1 ጀምሮ ካናዳ እና ሜክሲኮ ላይ የ25 ከመቶ ቀረጥ (ታሪፍ) ይጣላል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡
ከውጭ በሚገቡት የቻይናውያንን ምርቶች ላይ ግን ስለሚጥሉት የቀረጥ እቅዳቸው አልገለጹም፡፡
ትረምፕ ምክር ቤቱ ቲክ ቶክ ላይ የጣለውን እገዳ ለ75 ቀናት የሚያቆይ ትእዛዝ ፈርመዋል።
ቲክቶክ ከብሔራዊ ደህንነት ጋራ በተያያዘ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እንዲታገድ በባይደን አስተዳደር ጊዜ የወጣውን ሕግ አስመልክቶ ትረምፕ በሰጡት ምላሽ አስተዳደራቸው “ወደፊት ተገቢውን ውሳኔ እስኪሰጥበት ድረስ” የፍትህ ሚኒስቴር እገዳውን ተግባራዊ እንዳያደርግ አዘዋል፡፡
ታዋቂውን የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ በኩባንያው ውስጥ የሚኖረውን የባለቤትነት ድርሻ ዕድልን ጨምሮ ለአሜሪካውያን ክፍት ሆኖ እንዲቆይ በማድረግ፣ የብሔራዊ ደህንነት ጥቅሞችን በሚያስጠብቅ ስምምነት፣ የአሜሪካን ገዥ እንደሚያፈላልጉ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡
ትረምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ያደረጉትን በመድገም “የኮቪድ 19 ወረርሽኝን በአግባቡ ሳይቆጣጠር ከዩናይትድ ስቴትስ በርካታ የገንዘብ ድጋፍ አግኝቷል ካሉት ከዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት አሜሪካ እንድትወጣ አዘዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ዛሬ ማክሰኞ በሰጠው መግለጫ የትረምፕ ውሳኔ “እንዳሳዘነው” ገልጾ “በዓለም ዙሪያ ላሉ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች ጤና እና ደህንነት ”ከዩናይትድ ስቴትስ ጋራ ገንቢ ንግግሮችን ለማድረግ ያለውን ተስፋ ገልጿል፡፡
ትረምፕ የሜክሲኮ ባሕረ ሰላጤውን የአሜሪካ ባሕረ ሰላጤ ወደሚል የሚቀይር የአስፈጻሚ ትእዛዝ እንደሚፈርሙም አስታውቀዋል፡፡
ትረምፕ በባይደን አስተዳደር የነበሩ በርካታ የኢምግሬሽን ትእዛዞችን ሽረዋል፡፡
ከባድ ወንጀሎችን ለሚፈጽሙ፣ የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ተደርገው የሚወሰዱ ወይም ድንበር ላይ የሚያዙ ሰዎችን ከሀገር ማባረር ቅድሚያ ከሚሰጣቸው መካከል ናቸው፡፡
ሀገሪቱ ውስጥ በሕገወጥ መንገድ የሚገኝን ማንንም ሰው ማባረረ ቅድሚያ የሚሰጠው ነው የሚለው የመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ፖሊሲ አሁን ተመልሶል፡፡
በኢምግሬሽን ላይ ያተኮሩት የተለያዩ የትረምፕ አስፈጻሚ ትዕዛዝት፣ በዩናይትድ ስቴትስ-ሜክሲኮ ድንበር ላይ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ማወጅ፣ የጥገኝነት ጥያቄን (asylum) ማቆም እና ወላጆቾቻቸው የዩናይትድ ስቴትስ ዜጋ ያልሆኑና በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ለተወለዱ ህጻናት የሚሰጠውን (የተወላጅነት) ዜግነት ማቆም በመሳሰሉት ላይ ያተኮሩ ናቸው።
ትረምፕ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ መግባት የሚፈልጉት ሁሉ ማንነታቸው “እስከተቻለው ከፍተኛ መጠን” እንዲጣራ እና እንዲሁም መንግሥት፣ ዜጎቻቸው ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ለመከላከል ተገቢ የማጣራት ሂደት የማያደርጉትን ሀገራት እንዲለይ አዘዋል።
"የሕዝብ እና ብሄራዊ ደኅንነት" አንድምታው እስኪገመገም ድረስ የዩናይትድ ስቴትስ ፍልስተኞችን እንዳትቀበል ለጊዜው አግደዋል፡፡ ጥገኝነት ጠያቂዎች ሜክሲኮ ድንበር ውስጥ እንዲጠባበቁ የሚያስገድደውንም ፖሊሲ እንደገና ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡ ሜክሲኮ ፍልስተኞችን ለመቀበል ፈቃደኛ ስለመሆንዋ ግን ባለሥልጣናት አልተናገሩም፡፡
ትረምፕ በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው “አሜሪካ ትቅደም” የሚል መርህ ያለው የውጭ ፖሊሲን ተከትለዋል፡፡ ትላንት ሰኞ በፈረሙት የአስፈጻሚ ትእዛዝም አዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በዚህ ተልዕኮ ላይ እንዲያተኩሩ ትእዛዝ ሰጥተዋል።
አስፈጻሚው ትዕዛዝ "ከዚህ ቀን ጀምሮ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ፖሊሲ የአሜሪካን መሠረታዊ ጥቅሞችን ያስከብራል ሁልጊዜም አሜሪካን እና የአሜሪካን ዜጎች ያስቀድማል" ይላል፡፡
ትረምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው የወሰዱትን ርምጃ በመድገም ዩናይትድ ስቴትስ እ.ኤ.አ. ከ2015ቱ የፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነት እንድትወጣም አዘዋል። አሜሪካ ለሌሎች ሀገራት አርአያ መሆን የሚገባውን "ሁለቱንም ኢኮኖሚያዊ እና አካባቢያዊ አላማዎችን በማራመድ" የተሳካ ውጤት እንዳላት ትረምፕ ተናግረዋል ።
ስምምነቱን የተፈራረሙት ወደ 200 የሚጠጉ ሀገራት ናቸው፡፡ ስምምነቱ የዓለም ሙቀት መጨመርን ለመገደብ፣ እያንዳንዱ ሀገር ለአየር ንብረት ለውጡ አስተዋጽኦ የሚያደርገውን የከባቢ አየር ጋዝ ልቀት (greenhouse gas emissions) ለማስቆም፣ የሚያስችለውን እቅድ ማውጣት ነው፡፡
ፕሬዝዳንቱ በብሔራዊ ደኅንነት ረገድ፣ የቀድሞ የብሔራዊ መረጃ ዳይሬክተር ጄምስ ክላፐር፣ የሲአይኤ ዳይሬክተርና የመከላከያ ሚኒስቴር የነበሩት ሊዮን ፓኔታ፣ እና የራሳቸው የቀድሞ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጆን ቦልተንን ጨምሮ የነበራቸውን የሴኩዩሪቲ ክሊረንስ (የይለፍ ማረጋገጫ) አንስተዋል፡፡
ትራምፕ ከወታደራዊ እና ሌሎች የመንግሥት አካላት በስተቀር የፌደራል መንግስት ቅጥር አስቁመዋል። በባይደን አስተዳደር አዲስ የወጡ የፌደራል ደንቦችም ተግባራዊ እንዳይደረጉ አዘዋል፡፡
የፌደራል መንግስቱን የበለጠ ብቁና ውጤታማ ለማድረግ የመንግሥት ተቋማትን ያቀላጥፋል፣ አላግባብ ወጭዎችን የሚቀንሱበትን ምክር ያቀርባል የተባለው ተቋም ቀደም ሲል ማቋቋቸውም ተገልጿል፡፡ በምህጻሩ ዳጅ የተባለ አማካሪ ተቋም በዓለም ባለጸጋ በሆኑት ኢላን መስክ የሚመራ መሆኑ ተነግሯል፡፡
መድረክ / ፎረም