የአሜሪካ ጦር በፈጸመው የአየር ጥቃት 10 የአል ሻባብ አባላት መገደላቸውን የሶማሊያ መንግሥት አስታውቋል።
የሶማሊያ የማስታወቂያ ሚኒስቴር በመግለጫው እንዳለው፣ የአየር ጥቃቱ የተፈጸመው ቢርሃኒ በተባለና ከኪሲማዮ ሰሜን ምዕራብ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ሥፍራ ነው። የሚኒስቴሩ መግለጫ የወጣው ትላንት እሑድ ሲኾን፣ የአየር ጥቃቱ መቼ እንደተፈጸመ ግን አላሳወቀም።
የሶማሊያው የማስታወቂያ ሚኒስቴር። “ኻዋሪጅ (ወይም አፈንጋጮች) ጥቃት ለማድረስ በማቀድ ላይ ሳሉ ተደምስሰዋል። በጥቃቱ ሲቪሎች ላይ ጉዳት አልደረሰም” ብሏል
“የሶማሊያ ኅይሎች አሜሪካ ዋናው አካል ከሆነው ዓለም አቀፍ አጋር ጋራ በመተባበር ኻዋሪጆችን ለማጥፋትና በሶማሊያ ሕዝብ ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት ለመከላከል ቁርጠኞች ናቸው” ሲል አክሏል የማስታወቂያ ሚኒስቴሩ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሶማሊያ ጦር የአፍሪካ ዕዝ ዛሬ እንዳስታወቀው ከሶማሊያ መንግሥት ጋራ በመተባበር ባደረገው የአየር ጥቃት ሞሃመድ ሚሬ ወይም አቡ አብዲራህማን በሚል ስም የሚታወቅ ከፍተኛ የአል ሻባብ አመራር ዓባል ከሁለት ሳምንታት በፊት በተፈጸመ የአየር ጥቃት መግደሉን አረጋግጧል። የሶማሊያ መንግሥት ሞሃመድ ሚሬ መገደሉን ከአንድ ሳምንት በፊት አስታውቆ ነበር።
አፍሪኮም በአወጣው መግለጫ " ሚሬ በሌላ ስሙ አቡ አብዲራህማን ባለፉት 15 ዓመታት በአልሻባብ አገዛዝ ሥር ለዋሉት የሶማሊያ አካባቢዎች ኃላፊው ነበር " ብሎታል። ሚሬ ለአያሌ ዓመታት ከቆዩ የአልሻባብ አባላት አንዱ እንደነበረ የጠቀሰው መግለጫው በቡድኑ የሀገር አስተዳደር ሚኒስትርነት እንዲሠራ እና በቡድኑ ስልታዊ ውሳኔዎች ቁልፍ ሚና እንደነበረው መግለጫው አውስቷል። በተወሰደው ጥቃት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት አለመድረሱን መግለጫው አክሎ አመልክቷል።
የአሜሪካው የጦር ኃይል የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ማይክል ላንግሊ " በብሔራዊ ጸጥታ ስትራተጂያችን በዝርዝር እንደተመለከተው አሜሪካ የሚፈጠሩ የሽብርተኝነት ስጋቶችን በቁርጠኝነት መከላከሏን ትቀጥላለች" ማለታቸውን መግለጫው ጠቅሷል። እ አ አ የ2024 የዓለም አቀፍ የሽብርተኝነት ሰንጠረዥ ሽብርተኛ ቡድኖች ከባድ ዓለም አቀፍ ስጋት መሆናቸው መቀጠሉን አጉልቶ አሳይቷል። ከእነዚህ ስጋቶች መካከል አንዱ አልሻባብ ነው" ያለው መግለጫው " በቀጣናው ከእኛ ጋራ ተመሳሳይ አመለካከት ካላቸው አጋሮቻችን ጋራ ኾነን አልሻባብን እና ሌሎችንም አደገኛ አካላት እንዋጋቸዋለን" ብሏል። እነዚህን ድንበር ተሻጋሪ ስጋቶች በትብብር መታገል ለቀጠናው መረጋጋት እና ብልጽግና ይጠቅማል" ሲል አውስቷል።
አፍሪኮም ስለተካሄደው ጥቃት ለጊዜው በዝርዝር ከመናገር ተቆጥቧል።
መድረክ / ፎረም