ሚያንማር ከብሪታንያ ነጻ የወጣችበትን 77ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የሀገሪቱ ወታደራዊ መንግሥት ከ6 ሺሕ በላይ እስረኞች በምህረት ለቀቀ። የሌሎች እስረኞች ቅጣት መጠንም ቀንሷል።
ወታደራዊው መንግሥት በሕዝብ ከተመረጠው የኦንግ ሳን ሱ ቺን አስተዳደር ሥልጣን ከነጠቀበት የአውሮፓዊያኑ የካቲት 2021 ዓ.ም ጀምሮ በወታደራዊ አገዛዝ ከታሰሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች መካከል በአኹኑ ምህረት የተካተቱት ጥቂቶቹ ናቸው።
ወታደራዊው አገዛዝ ሥልጣን ላይ የወጣበት ሂደት በወቅቱ ከፍተኛ ሰላማዊ ተቃውሞ የገጠመው ሲኾን ፣ አሁን ላይ ግን ወደተንሰራፋ የትጥቅ ትግል ተቀይሯል።
በመንግሥት የሚተዳደረው ኤምአርቲቪ ቴሌቪዥን የወታደራዊው መንግሥት መሪ ከፍተኛ ጄኔራል ሚን አንግ ህላይንግ፣ለ5 ሺሕ የሀገሪቱ ዜጋ እስረኞች እንዲሁም 180 የውጭ ዜጎች ምህረት እንዳደረጉ ዘግቧል። በሚያንማር በበዓላት እና በጉልህ ሁነቶች ወቅት እስረኞችን በብዛት መልቀቅ የተለመደ ነው።
ከእስር የተፈቱት እስረኞች እንደገና ሕጉን ከጣሱ፣ ከአዲስ ቅጣት በተጨማሪ ቀሪውን የቅጣት ፍርዳቸውን እንዲጨርሱ እንደሚደረግ በምህረት የተለቀቁበት ቅደመ ሁኔታ ያስጠነቅቃል።
በሌላ ዘገባ ሚን አውንግ ህላይንግ የ144 እስረኞችን የዕድሜ ልክ እስራት ወደ 15 ዓመት እስራት ዝቅ እንዲል መወሰናቸው ተሰምቷል። ዘገባው በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።
በጸረ - ፈንጂ፣ በሕገ-ወጥ ማኅበራት፣ በጦር መሳሪያ እና በፀረ-ሽብርተኝነት ሕግ ከተከሰሱት በስተቀር ሁሉም እስረኞች ቅጣታቸው በአንድ ስድስተኛ እንደሚቀነስላቸው ዘገባው አክሏል።
የወታደራዊ መንግሥት ቃል አቀባይ ሜጀር ጄኔራል ዛው ሚን ቱን ፣ለጋዜጠኞች በተውት የድምጽ ማስታወሻ፣ ከእስር ከተፈቱት መካከል ወደ 600 የሚጠጉ እስረኞች በሚያንማር የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀፅ 505(A) የተከሰሱ መሆናቸውን ተናግረዋል ። አንቀጹ ሕዝባዊ ብጥብጥ ወይም ስጋት መፍጠር፣ ሐሰተኛ ዜና እና አስተያየቶች ማሰራጨትን በወንጀልነት ይደነግጋል።
መድረክ / ፎረም