ዩክሬን በሩሲያ ኦርዮል ግዛት ውስጥ የሚገኘውን የረጅም ርቀት ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ማከማቻ እና የጥገና መጋዘን መምታቷን ዛሬ ቅዳሜ ተናግራለች።
በዚህ ጥቃት ሩሲያ በዩክሬን ላይ በጅምላ የምትፈጽመውን መጠነ ሰፊ የድሮን ጥቃት “ በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ” ማድረጓንም ዩክሬን አክላለች፡፡
የዩክሬን ጦር ጠቅላይ ኤታማዦር በማህበራዊ መድረኩ ቴሌግራም ላይ የወጣው መግለጫ እንዳመለከተው ጥቃቱ የተፈፀመው ከትላንት በስቲያ ሐሙስ በዩክሬን አየር ኃይል ነው፡፡
መግለጫው አክሎ "በጥቃቱ ሳቢያ ከጥቃት ተጠብቀው የተከለሉ የካሚካዜር ድሮኖች ማከማቻ፣ የጥገና እና እድሳት፣ እንዲሁም ጥበቃ ይደረግላቸው የነበሩ በርካታ የኮንክሪት ግንባታዎች ወድመዋል” ብሏል ፡፡
"ይህ ወታደራዊ ዘመቻ የጠላት ኃይል በዩክሬን የሲቪል መሰረተ ልማቶች ላይ የአየር ላይ እና የድሮን ጥቃቶች የማድረስ አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል” ሲልም መግለጫው አክሏል፡፡
ሞስኮ ስለ ጥቃቱ ምንም አይነት አስተያየት አልሰጠችም፡፡
ሩሲያ በ34-ወራቱ የዩክሬን ወረራዋ በየጊዜው የሚሳይል እና ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ጥቃት ፈጽማለች።
ላለፉት በርካታ ወራት ሞስኮ በየቀኑ በዩክሬን በርካታ የሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃቶችን በመፈጸም የመሠረተ ልማት አውታሮች እና የአየር መከላከያዎችን በማዳከም በሚሳይሎቿ ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመቀነስ ተስፋ አድርጋለች፡፡
የዩክሬን አየር ኃያል ዛሬ ቅዳሜ ጧት ሌሊቱን ከተተኮሱ ከ16 የሩሲያ ድሮኖቹ አንደኛው ከራዳር እይታ ውጭ ሲሰወር 15ቱን መትቶ መጣሉን አስታውቋል፡፡
መድረክ / ፎረም