የደቡብ ኮሪያ አቃቤ ህግ ባለፈው ሳምንት የወጣውንና በአጭሩ የተቀጨውን ወታደራዊ ሕግ እንዲያውጁ ለፕሬዚዳንት ዮን ሱክ ዮል ሀሳብ ያቀረቡትን የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትር በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል፡፡
የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር ኪም ዮንግ ዩን ዛሬ እሁድ በገዛ ፈቃዳቸው በሴኡል አቃቤ ህግ ቢሮ ቀርበው በቁጥጥር ስር እንደዋሉ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል፡፡ ከወታደራዊ ህጉ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉ የመጀመርያው ሰውም ሁነዋል፡፡
እስሩ የመጣው ፕሬዘዳንት ዮን ከስልጣን እንዲነሱ በፓርላማ በተቃዋሚዎች የቀረበባቸውን ክስ ውድቅ ከሆነ በኋላ ነው፡፡ ዋናው ተቃዋሚ ዴሞክራቲክ ፓርቲ በዩን ላይ አዲስ የክስ መቃወሚያ እንደሚያዘጋጅም ተናግሯል።
አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የህግ አስከባሪ ባለስልጣን የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትር ኪም ዮንግ ዩን በሴኡል ማቆያ ጣቢያ በአቃቤ ህግ ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ለአሶሽየትድ ፕሬስ ገልጸዋል፡፡
ኪም በፕሬዘዳንት ዮን ወታደራዊ ህግ ላይ ዋና ሰው የነበሩ ሲሆን ህጉ ለመጽደቅ ቀርቦ በነበረበት ወቅትም የምክር ቤቱን ህንፃ በወታደሮች እንዲከበብና ወታደራዊ ሄሊኮፕተሮች በላዩ ላይ እንዲያንዣብቡ አድርገው እንደነበርም ተገልጿል፡፡
ምክርቤቱ አዋጁን በሙሉ ድምጽ ውድቅ ካደረገ በኋላም ወታደራዊ ሃይሎች ምክር ቤቱን ለቀው ወጥተዋል፡፡ ይህን ተከትሎ ሃሙስ እለት ኪም ያቀረቡትን የስራ መልቀቂያ ጥያቄ በፕሬዘዳንቱ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡
የሃገር ውስጥ ሚድያ ሪፖርቶቹ ዛሬ ፖሊስ የኪምን የቀድሞ ቢሮ እና መኖሪያ ቤት እንደፈተሸ ተናግረዋል። አሶሼትድ ፕሬስ ለተጨማሪ መረጃ ወደ ሴኡል አቃቤ ህግ ቢሮዎች እና የፖሊስ ኤጀንሲ ላደረጋቸው ተደጋጋሚ ጥሪዎች ምላሽ አላገኘም።
መድረክ / ፎረም