የሶሪያ አማፂያን ከመሃል ከተማዋ ሆምስ በስተሰሜን ያሉ ሁለት ከተሞችን ዛሬ መቆጣጠራቸውን የተቃዋሚ አቀንቃኞችና የመንግሥት ደጋፊ ብዙኅን መገናኛዎች አስታውቀዋል።
ራስታን እና ታልቢሰህ የተባሉት ከተሞች በቁጥጥር ሥር የዋሉት አማጺያኑ ሃማ የተባለችውን የሃገሪቱ ማዕከላዊ ከተማ ከተቆጣጠሩ ከአንድ ቀን በኋላ ነው። የሶሪያ ጦር በበኩሉ የከተማ ውስጥ ውጊያ ላለማድረግና የሲቭሎችን ሕይወት ለመታደግ ሲል ከተማዋን ለቆ መውጣቱን አስታውቋል።
ሃያት ታህሪር አል-ሻማ በተባለ መሪ ስም የሚጠራው የአማጺያን ቡድን ወደ ሆምስ እንዲሁም የፕሬዝደንት የባሽር አላሳድ መቀመጫ ወደ ሆነችው ደማስቆ ግስጋሴውን እንደሚቀጥል አስታውቋል። ሆምስ የተወሰነ ክፍሏ ላለፉት 10 ዓመታት በአማፂያን ቁጥጥር ሲሆን፣ በሶሪያ ትልቋ ከተማ ነች፡፡ ከሌባኖስ፣ ኢራቅ እና ዮርዳኖስ ጋራም ትዋሰናለች፡፡ አሁን በመገስገስ ላይ ያለው የአማፂ ቡድን ከሆምስ 5 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ እንደሚገኝ በእንግሊዝ መሠረቱን ያደረገና ጦርነቱን በቅርበት የሚከታተል የሶሪያ ተቃዋሚ ቡድን አስታውቋል። ሆምስን ለመቆጣጠር የሚደረገው ፍልሚያ ወሳኝ እንደሆነና ሶሪያን ማን እንደሚገዛ የሚወስንም እንደሆነ ቡድኑ አስታውቋል።
አማፂያኑ በቅርቡ ጥንታዊ የንግድ ማዕከል የነበረችውን አሌፖን ድንገት መቆጣጠራቸው፣ በሶሪያ ረግቦ የነበረውን ግጭት እንደገና አቀጣጥሏል።
መድረክ / ፎረም