በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አማፅያን እና አጋሮቻቸው አብዛኛውን የአሌፖ ክፍል መቆጣጠራቸውን የሶሪያን ጦርነት በቅርብ የሚያጠና ተቋም አስታወቀ


ተቃዋሚ ሃይሎች ከሶሪያ አሌፖ ከተማ ዳርቻ ያሉ አካባቢዎችን ተቆጣጠሩ።
ተቃዋሚ ሃይሎች ከሶሪያ አሌፖ ከተማ ዳርቻ ያሉ አካባቢዎችን ተቆጣጠሩ።

አማጺያን የሶሪያ ተዋጊዎች ከ2016 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የሶሪያን ግዙፍ ከተማ አሌፖን መቆጣጠራቸውን የሶሪያን ጦርነት የሚከታተለው ተቋም በዛሬው ዕለት አስታውቋል ። ጦርነቱ በቀጠለበት በአሁኑ ሰዓት የመንግስት ሃይሎች እና የሩሲያ የጦር አውሮፕላኖች በከተማይቱ የተለያዩ ስፍራዎች ላይ የአየር ጥቃት መፈጸማቸው ተገልጿል።

በጦርነት በተመሰቃቀለችው ሀገር ዙሪያ ጥናቶችን የሚያከናውነው ተመራማሪዎችን ያቀፈው የሶሪያ የሰብዓዊ መብቶች ታዛቢ የተሰኘው ተቋም እንዳስታወቀው በአልቃይዳ የቀድሞ የሶሪያ ቅርንጫፍ የሚመራው የጂሃዲስት ህብረት እና አጋር አንጃዎች የአሌፖን ከተማ አብዛኛው ክፍልን ፣ የመንግስት ማዕከላትን እና ማረሚያ ቤቶችን ተቆጣጥረዋል።


የአማፂ ኃይሎች ከሶሪያው ፕሬዝዳንት ባሻር አል አሳድ መንግስት ታማኝ ኃይሎች ጋር ከታዋጉ በኃላ አርብ ዕለት ወደ በከተማይቱ አንዳንድ ክፍሎች መግባታቸውን ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ በአሌፖ የሚገኙ እማኞች ለቪኦኤ አረጋግጠዋል።

የሶሪያ የሰብዓዊ መብቶች ታዛቢ ተቋም ከረቡዕ ጀምሮ በተቀሰቀሰው ግጭት 277 ሰዎች መሞታቸውን እና አብዛኞቹ አማፂያን እና የሶሪያ ወታደሮች እንደሆኑ አስታውቋል።

ይሁን እንጂ የተባበሩት መንግስታት የሶሪያ ቀውስ ምክትል የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ዴቪድ ካርደን በትናንትናው ዕለት እንደተናገሩት በጦርነቱ ህጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 27 ንፁሀን ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል።


የሶሪያ ጦር አርብ ባወጣው መግለጫ ፣በአሌፖ እና ኢድሊብ ገጠራማ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱት ሀይሎቹ በአሸባሪ ድርጅቶች የተሰነዘረውን ከባድ ጥቃት መመከት መቀጠላቸውን አስታውቋል ። ጦር ሰራዊቱ በአሌፖ ከተማ ስላለው ሁኔታ የሰጠው መግለጫ የለም።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG